አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኙት ‹‹Centre for Crop Health and Protection /CHAP›› እና ‹‹SWaDE Technology Company›› ጋር በመተባበር በጋሞ ዞን ጋርዳ ማርታ ወረዳ ቦሄ ቀበሌ ባዞ ወንዝ ላይ ለመስኖ አገልግሎት የሚውል 3.3 ኪሎ ዋት ኃይል የሚያመነጭ በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የኃይል ማመንጫ ተከላ አድርጓል፡፡ ተከላው ሦስቱ ተቋማት ‹‹Optimizing Energy Demand in Rural Communities via Precision Agriculture Technology›› በሚል ርእስ እያከናወኑ የሚገኙት የምርምርና ልማት ፕሮጀክት የሙከራ ሥራ ነው፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የ‹‹SWaDE Technology Company›› መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሌንሳ ኢተፋ ድርጅታቸው መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገና የሳታላይት መረጃዎችን በመጠቀም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን የሚያመርት እንዲሁም በኢነርጂ፣ ውኃ እና ምግብ ትስስር ላይ አተኩሮ የሚሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ሌንሳ በዚህ የትብብር ፕሮጀክት ኩባንያው ያፈለቀው SWaDE/Satellite based Water Demand Estimation/ የተሰኘ አዲስ ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩ የመስኖ ውኃ በሚጠቀም ጊዜ ተገቢውን የውኃ መጠን እንዲጠቀም በማድረግ ምርታማነትን የሚያሳደግ እንደሆነም ዶ/ር ሌንሳ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ሌንሳ ገለጻ በአብዛኛው መሰል ፕሮጀክቶች ለከተሞች አጎራባች በሆኑ አካባቢዎች የሚሠሩ ሲሆን በአንጻሩ ይህ ፕሮጀክት ከዋና መንገድም ሆነ ከኤሌክትሪክ መስመር ለራቀው ማኅበረሰብ ተመጣጣኝና ዘላቂ የታዳሽ ኃይል ለማቅረብ የሚሠራ በመሆኑ የተለየና ጠቀሜታውም በእጅጉ የጎላ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ አሁን ላይ የተሠራው የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ የሙከራ ሥራ ሲሆን በቀጣይ የቴክኖሎጂውን ውጤታማነት በመፈተሽ በአካባቢው ለማስፋፋት እንደሚሠራ ዶ/ር ሌንሳ ጠቁመዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ የጋርዳ ማርታ ወረዳ በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቃ አካባቢ በመሆኑ ፕሮጀክቱ በፀሐይ ኃይል ተጠቅሞ በአካባቢው የሚገኝ ወንዝን በመሳብ አርሶ አደሩ ዝናብ ጠብቆ ከማረስ በዘላቂነት እንዲወጣ ጥናትን መሠረት አድርጎ የተተገበረ የሙከራ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሙከራ ፕሮጀክቱ በስኬት መጠናቀቁ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ በሚከሰት ድርቅ ከሚደርስበት ጉዳት በማላቀቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ ከዚህም ባሻገር ፕሮጀክቱ በቀጣይ ሊሠሩ የታሰቡ ሰፊ ፕሮጀክቶች በቀላሉ እንዲገኙ በር የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡ በፕሮጀክቱ የተሠሩና በቀጣይ ተግባራዊ የሚሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ከዩኒቨርሲቲው ተልእኮ ጋር የተስማሙ ከመሆናቸው ባሻገር የሀገሪቱን የግብርና ሥራ የሚያዘምኑ እንዲሁም በመስኩ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት የሚፈቱ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ  ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ጊዜያትም ከአካባቢና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ጋር የተስማሙ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶችን ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ተባብሮ መሥራቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ተ/ፕ በኃይሉ ጠቁመዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ተመራማሪና የፕሮጀቱ አስተባባሪ አቶ በየነ ፈዬ በጋርዳ ማርታ ወረዳ ቦሄ ቀበሌ የሚገኙ አርሶ አደሮች በናፍጣ የሚሠሩ ፓምፖችን በመጠቀም መሬታቸውን በመስኖ ለማልማት የሚጥሩ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የነዳጅ ዋጋ ምክንያት ለችግር ተዳርገው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር አካባቢው በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቃና የምግብ ዋስትና ችግር የሚታይበት እንደመሆኑ አርሶ አደሩ ታዳሽ ኃይልን ለውኃ መሳቢያነት ተጠቅሞ መሬቱን በመስኖ እንዲያለማ ማስቻል የፕሮጀክቱ ዓለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ በየነ አክለውም በአካባቢው አዲስ የተተከለው 3.3 ኪሎ ዋት የሚያመነጨው የሶላር ኃይል ማመንጫ ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ የናፍጣ ፓምፖችን ከአካባቢው ጋር ተስማሚ በሆነው ታዳሽ ኃይል የሚተካ ነው፡፡ በፕሮጀክቱ የተተከለው የፀሐይ ኃይል ማመንጫ የመጀመሪያ ሙከራ/pilot/ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው በዚህም 17 ሄክታር መሬት በማልማት 30 አባወራዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡ በአካባቢው በመስኖ ሊለማ የሚችል ከ200 ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት መኖሩን በዚሁ ፕሮጀክት በተደረገ ጥናት መረጋገጡን የገለጹት አቶ በየነ ተባባሪ አጋር አካላትን አፈላልጎ የገንዘብ በማግኘት የሙከራ ሥራውን ማስፋት የፕሮጀክቱ ቀጣይ ግቦች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አንድ ሰብል በመስኖ ለማልማት ምን ያህል ውኃ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ይፈልጋል የሚለውን ጉዳይ መለየትና ስታንዳርድ ማስቀመጥ የትብብር ፕሮጀክቱ ሌላኛው ትኩረት እንደነበር የገለጹት አቶ በየነ በዚህም የሰብሉን ዓይነትና የአካባቢውን የአየር ሁኔታ ከግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ የውኃ መጠን ስታንዳርድ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ ይህም በውኃ መጠን መብዛትና ማነስ የሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮችን የሚቀርፍ እንደሆነ ተመራማሪው አክለዋል፡፡

የጋርዳ ማርታ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ባሕርዛፍ ፋንታዬ በበኩላቸው አካባቢው በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት ቢኖረውም በተደጋጋሚ በሚከሰት ድርቅ ምክንያት አርሶ አደሮቻችን ለችግር ሲዳረጉ ቆይተዋል ብለዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ከፀሐይ ኃይል በሚገኝ ኢነርጂ የእርሻ መሬቶችን በመስኖ ለማልማት ከጀመረው ፕሮጀክት የሚገኙ አዳዲስ ልምዶችና አሠራሮች አካባቢውን በዘላቂነት በድርቅ ምክንያት ከሚከሰት የምግብ እጥረት የሚያላቅቀውና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዝ እንደሆነም አቶ ባሕርዛፍ ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱን ለማስቀጠልና ለማስፋት ለሚደረጉ ጥረቶች የወረዳው መንግሥትና ሕዝብ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ከአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ዳርቆሌ ሚራሞ ከዚህ ቀደም የአካባቢው አርሶ አደሮች በተወሰነ ደረጃ መሬታቸውን ለማልማት በነዳጅ የሚሠራ ፓምፕ ሲጠቀሙ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ የመጣ በመሆኑ ወጪና ገቢያቸው ሊመጣጠን ባለመቻሉ በእጅጉ መቸገራቸውንና ሥራውን ለማቆም አስበው እንደነበርም አቶ ዳርቆሌ ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለነዳጅ የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪ የሚያስቀር በፀሐይ ኃይል የሚሠራ ቴክኖሎጂ እንድንጠቀም ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ በእጅጉ አስደስቶናል ብለዋል፡፡ ወደፊትም ዕድሉን በመጠቀም መሬታቸውን ሙሉ በሙሉ ለማልማት መዘጋጀታቸውንና ቲማቲም፣ ሽንኩርትና ሀባብ የመሳሰሉ የግብርና ውጤቶች በተጨማሪነት ለማምረት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት