አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 11ኛውን ዓመታዊ የምርምር ወርክሾፕ የካቲት 30/2016 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓላማቸውን ከማሳካት ባሻገር የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታትና ለሳይንስ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ የምርምር ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ሥራዎችን በብዛትም ሆነ በጥራት በማሻሻል አቅሙን እያጎለበተ ይገኛል ያሉት ዶ/ር ዳምጠው የመምህራንና የተመራማሪዎችን ክሂሎት ለማሳደግ ሥልጠና መስጠት፣ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞችን መክፈትና ማሳደግ እንዲሁም የምርምር ሂደት መመሪያንና የውስጥ ጆርናሎችን ማጠናከር የዩኒቨርሲቲውን የምርምር ሥራ አቅም ለማሳደግ እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በዓመቱ ውስጥ እያንዳንዱ ኮሌጅ፣ የምርምር ማዕከል እና ተመራማሪዎች በተለያዩ ደረጃዎች በምርምር እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ በወርክሾፑ በየመስካቸው ሳይንሳዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸው ጥናቶች የሚቀርቡ ሲሆን ከተለያዩ ዘርፎች የተወጣጡ ተመራማሪዎች፣ ምሁራንና ባለሙያዎች እርስ በእርስ የሚማማሩበት፣ ግንዛቤ የሚለዋወጡበት እንዲሁም ለጋራ ዕውቀት እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት መድረክ ነው፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በበኩላቸው በወርክሾፑ ከሚቀርቡ 660 ጥናትና ምርምሮች 110ሩ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁና 550ዎቹ በሂደት ላይ ያሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከተጠናቀቁ ምርምሮች መካከል ሦስቱ ዋናና ወቅታዊ ችግሮች ላይ የተጠኑ ጥናቶች ለመክፈቻነት የቀረቡ ሲሆን ቀሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ስድስቱም ካምፓሶች በሚገኙ ኮሌጆች፣ ኢንስቲትዩቶችና ትምህርት ቤቶች እስከ መጋቢት 07/2016 ዓ/ም እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ በወርክሾፑ ያለቁ ምርምሮች ከነውጤታቸው እንዲሁም ያላለቁና በሂደት ላይ ያሉ ምርምሮች ካጋጠሙ ችግሮቻቸው ጋር ቀርበው እንደሚገመገሙ የተናገሩት ዶ/ር ተስፋዬ ያላለቁ ምርምሮችን ችግሮቻቸውን ለይቶ ድጋፍና ክትትል ማድረግ የወርክሾፑ ዓላማ ነው ብለዋል፡፡

በወርክሾፑ የጋራ መድረክ ‹‹Assessment of Geotechnical Problems on the Arba Minch Geressie-Kamba-Sawla Road››  Project (Shele Mela to Sawla Road Section)›› በአቶ ደፋሩ ካትሴ፣ ‹‹The Dynamics of Markets Of Cultural Identity in Gamo and Konso Zone, Ethiopia›› በዶ/ር ካሌብ ካሳና ‹‹Challenges and Practices of Service Delivery Quality Evidence From Gamo Zone Some Selected Public Sectors›› በአቶ ቢክስ ሰጠኝ ቀርበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሲቪል ምኅንድስና ፋከልቲ መምህርና ተመራማሪ ረ/ፕ ደፋሩ ካትሴ ‹‹Assessment of Geotechnical Problems on the Arba Minch-Geressie-Kamba-Sawla Road Project (Shele Mela to Sawla Road Section) በሚል ርእስ የተሠራ ጥናታቸውን ያቀረቡ ሲሆን የአፈሩ ዓይነት ደካማ (Soft) መሆን፣ ከየሸለቆው የሚወርደው ውኃና የአካባቢው መልክአ ምድር በመንገዱ ላይ ከፍተኛ ችግር እያመጣ እንደሆነና በመንገዱ አሠራር ሂደት ላይ መሠረታዊ ችግር እንዳለ በጥናቱ መለየቱን ገልጸዋል፡፡ የምርምር ውጤቱ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ለመንገዱ መፍትሔ እንዲፈለግና ፖሊሲ አውጪዎች መረጃውን ተጠቅመው ግብዓት እንዲያደርጉት ጥቆማ መስጠታቸውንም ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት