የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ 2 ደረጃ ትምህርት ቤት 12 ክፍል ተማሪዎች የአብሥራ ፍፁም እና ዳግም ሰለሞን የመምህራን ሰዓት መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ሠርተው መጋቢት 4/2016 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲውና የት/ቤቱ አመራሮች በተገኙበት አቅርበዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ተማሪ የአብሥራ ፍፁም እና ዳግም ሰለሞን ሶፍትዌሩን ለመሥራት አራት ዓመት የፈጀባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡   መምህራን ለአንድ ክፍለ ጊዜ የተሰጣቸውን 40 ደቂቃ በአግባቡ እየተጠቀሙ አለመሆኑ ሶፍትዌሩን ለመሥራት ያነሳሳቸው መሆኑን የገለጹት ተማሪዎቹ ሶፍትዌሩ ይህንን ችግር ለማስተካከል የሚረዳ እንደሆነም አክለዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት ተማሪዎች በት/ቤት ቆይታቸው ከችግሮች በመነሳትና በራስ ተነሳሽነት ችግር ፈቺ የሆነ ቴክኖሎጂ መሥራታቸው የሚበረታታ ነው፡፡ ተማሪዎቹ አራት ዓመት መሉ ዋጋ ከፍለው ይህን ቴክኖሎጂ መሥራታቸው የሚያስመሰግናቸው መሆኑን የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ የተማሪዎቹ ጥረት ለሌሎች ተማሪዎች ትልቅ ተሞክሮና ተነሳሽነትን የሚፈጥር ነውም ብለዋል፡፡  ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን በመደገፍ የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ እንደሚሠራም ም/ፕሬዝደንቱ አክለው ተናግረዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የፈጠራ ሃሳብ ከትንሽ ወደ ትልቅ ደረጃ እያደገ የሚሄድ በመሆኑ ተማሪዎቹ የሠሩት ቴክኖሎጂ የት/ቤቱን ችግር ብቻ ሳይሆን በሀገር ደረጃ የሚታየውን የሥራ ባህል ችግር የሚፈታ መሆኑን  ጠቁመዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና በበኩላቸው ተማሪዎቹ የት/ቤቱን ችግር በማወቅ የመፍትሔ አካል በመሆን በራሳቸው ተነሳሽነትና ጥረት ይህን የመሰለ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂ ማቅረባቸው የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ ቴክኖሎጂን ለማይረባ ነገር የሚጠቀሙ ወጣቶች እንዳሉ ሁሉ በዚህ ልክ ቴክኖሎጂን ለሚጠቅም ነገር የሚጠቀሙ ወጣቶችን ማየት መቻሉ በራሱ አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት