አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ‹‹Dereja Academy Accelerator Program/DAP›› ጋር በመተባበር በጋሞ ዞን ለሚገኙና በ2014 ዓ/ም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ሥራ ላጡ ወጣቶች ራስን ማወቅና ተግባቦት የመሳሰሉ ሰዋዊ ክሂል /Soft Skill/ እንዲሁም በትምህርት ማስረጃ /CV/ አዘገጃጀት ዙሪያ ከመጋቢት 5-12/2016 ዓ/ም የሚቆይ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል አስተባባሪ መ/ርት ስለእናት ድሪባ እንደገለጹት መጋቢት 15/2016 ዓ/ም በተለያዩ መስኮች የሚሠሩ ከ50 በላይ ድርጅቶችን በመጋበዝ በሚደረገው የሥራ ዐውደ ርእይ ላይ በመሳተፍ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው በማሰብ ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ ተመርቀው ሥራ በመፈለግ ላይ ላሉ ከአርባ ምንጭ ከተማና ከጋሞ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ ወጣቶች ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ የሚካሄደው የደረጃ ዶት ኮም እህት ኩባንያ/Dereja.Com Sister Company/ የሥራ ዐውደ ርእይ/Job Fair/ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሊኒየም አዳራሽ በየዓመቱ እንደሚካሄድ የተናገሩት አስተባባሪዋ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ለማስፋፋት ከተለያዩ ከተሞችና ድርጅቶች ተወካዮችን በመጋበዝ የሚዘጋጅ መድረክ ነው ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሥነ ሕንፃና ከተማ ፕላን ፋከልቲ መምህራን የሆኑት በእምነት ካሳዬ እና ዓለሜ ግርማ ተመራቂ ተማሪዎችን ከቀጣሪ ካምፓኒዎች ጋር ለማገናኘት የዶክመንት አዘገጃጀት እና የ ‹‹Cover letter››፣ ‹‹CV››፣ ‹‹Resume›› እና ‹‹letters of recommendation›› አጻጻፍ ዙሪያ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ ሠልጣኞች የትምህርት ማስረጃዎችን በጥራት በማዘጋጀት በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም መስኮች ሥራ ማግኘት ይችሉ ዘንድ ራሳቸውን ማዘጋጀትና መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው አሠልጣኞቹ አሳስበዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በግብርና ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀችው ወጣት ወይንሸት ወንድሙ ሥልጠናው ራሴን በይበልጥ እንዳውቅና የሥራ ዕድል ለመፍጠር በምን መልኩ መዘጋጀት እንዳለብኝ አሳይቶኛል ብላለች፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት