የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ከደረጃ ዶት ኮምና ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባባር ‹‹Arba Minch Job Fair›› በሚል ርእስ የመጀመሪያውን የሥራ ዐውደ ርእይ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መጋቢት 14/2016 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የሀገራችን የትምህርት ሥርዓት ከጥራት አንጻር ከዝቅተኛ ትምህርት ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ድረስ ከፍተኛ ችግር እንዳለበትና ለዚህም በ2014 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች ሦስት በመቶው ብቻ እንዲሁም በሀገራዊው የመውጫ ፈተና 40 ከመቶ ተመራቂዎች ብቻ ማለፋቸው እንደ ማሳያ ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡ በጥሩ ውጤት ያለፉ ጥቂት ተማሪዎችም ቢሆኑ የሥራው ዓለም የሚፈልገውን ክሂሎትና አመለካከት የተላበሱ ባለመሆኑ እንደሚቸገሩ በተለያዩ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚሰጥ አስተያየት ነው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ክፍተቱን ለመሙላት ደረጃ ዶት ኮም ላለፉት በርካታ ዓመታት ተመራቂ ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲ እያሉ ለሥራ ዓለም ብቁ የሚያደርጓቸው ክሂሎቶችን እያሠለጠነና ቀጣሪና ተቀጣሪ የሚገናኙበትን መድረክ እያዘጋጀ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዓለማየሁ ተመራቂ ተማሪዎችን ወደ ሥራ ዓለም ማሠማራት እንደ ሀገር ለአንድ ድርጅት የሚተው ጉዳይ ባለመሆኑ የሁሉንም ተሳትፎና ኃላፊነት የሚጠይቅ ነው፡፡  መሰል የሥራ ዐውደ ርእይ መዘጋጀቱ ቀጣሪና ተቀጣሪን በአንድ ቦታ በማገናኘት ጊዜ፣ ጉልበትና የገንዘብ ወጪን በመቆጠብ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል አስተባባሪ መ/ርት ስለእናት ድሪባ ማዕከሉ ከድርጅቱ ጋር እ.ኤ.አ ከ2017 ጀምሮ የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈራረም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተመርቀው ከመውጣታቸው በፊት እንዲሁም በአርባ ምንጭ ከተማና በጋሞ ዞን ወረዳዎች ለሚገኙ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አዲስ ለተመረቁ ወጣቶች ለሥራ ዝግጁነት የሚረዱ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ የደረጃ ዶት ኮም ሥልጠና መሳተፍ የሚፈልጉ አዲስ ምሩቃን ማስታወቂያዎችን ከዩኒቨርሲቲው ዌብሳይት፣ ቴሌግራምና ፌስቡክ ገጾች በመከታተል መመዝገብ እንደሚችሉ አስተባባሪዋ ጠቁመዋል፡፡ የሥራ ዐውደ ርእዩ ተቀጣሪዎች የሚፈልጉትንና ከትምህርት ዝግጅታቸው ጋር የሚስማማውን የሥራ መስክ እንዲያገኙ እንዲሁም ቀጣሪ ድርጅቶች የሚፈልጉትን ሙያዊ ክሂሎት ያለው ባለሙያ በአንድ መድረክ እንዲያገኙ የሚረዳ እንደሆነ አስተባባሪዋ ገልጸዋል፡፡

የደረጃ ዶት ኮም የትብብር ማኔጀር ወ/ሮ ሉዋም ፍሥሃዬ እንደገለጹት ድርጅቱ ከአፍሪካ ኔትወርክ ካምፓኒ ጋር በመተባባር ለአዲስ ምሩቃን ተለያዩ ሥልጠናዎችን የሚሰጥ ሲሆን ሥልጠናውን የወሰዱ ምሩቃንን ከቀጣሪ ደርጅቶች ጋር በማገናኘት የሥራ ዕድል እንዲያገኙ እንዲሁም ቀጣሪ ድርጅቶች የሚፈልጉትን ሰዋዊና ሙያዊ ክሂሎት የተላበሱ ባለሙያዎችን እንዲያገኙ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ይሠራል፡፡ የሥራ ዕድሉን ለማመቻቸት ድርጅቱ የሥራ ዐውደ ርእይ/job fair/Career fair/ የሚያዘጋጅ ሲሆን ከ50 በላይ ቀጣሪ ድርድቶችን በመጋበዝ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው ዐውደ ርእይ ከአርባ ምንጭ ከተማና ከጋሞ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ከ1,000 በላይ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚያገኙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኘው ነጭ ሣር ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያና የማስታወቂያ ሥራ ክፍል ኃላፊ አቶ አስታጥቅ አበራ ሆስፒታሉ በከተማው የሚገኝ ብቸኛው የግል ሆስፒታል መሆኑን ጠቁመው የሰው ኃይል ክፍተቱን ለማሟላት በሕክምናና በኮምፕዩተር ሳይንስ የተመረቁ ባለሙያዎችን ለመቅጥር አስበው በሥራ ዐውደ ርእዩ መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዐውደ ርእዩ ከጠበቁት በላይ የተለያዩ ባለሙያዎችን በአንድ ቦታ በአንድ ቀን በማግኘታቸው መደሰታቸውን የገለጹት አቶ አስታጥቅ በሆስፒታላቸው ለመቀጠር በርካታ ምሩቃን መመዝገባቸውንና ምልመላውን ሲጨርሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሰጡት አድራሻ ጠርተው ቅጥር እንደሚፈጽሙ ገልጸዋል፡፡

ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂና የደረጃ ዶት ኮምን ሥልጠና የወሰደችው ወጣት ብርሃን ደጀኔ ሥራ ፈላጊ ሆና በዐውደ ርእዩ መገኘቷንና ከትምህርት ዝግጅቷ ጋር በሚገናኙ ሥራዎች የተለያዩ ድርጅቶች ጋር ተመዝግባ ውጤቷን እየተጠባበቀች እንደምትገኝ ተናግራለች፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት