የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ለመጡ ባለሙያዎች ምርትና ምርታማነትን መደገፍ በሚያስችሉ የግብርና ቴክኖሎጂና ሞዴሎች ዙሪያ “Decision Support System for Agro-technology Transfer/DSSAT” በሚል ርዕስ ከሚያዝያ 16-19/2016 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም በሥራ ዓለም ለሚገኙ ሰዎች ወቅታዊ፣ በቀጥታ ከሥራቸው ጋር  የሚገናኙና ሥራን የሚያቀላጥፉ ሥልጠናዎች ያስፈልጋሉ ያሉት ዶ/ር ቦጋለ የመጀመሪያ ዙር ሠልጣኞች የተሰጣቸውን ሥልጠና በአግባቡ ተግባር ላይ በማዋል ድጋፋቸውን ለሚፈልጉ አርሶ አደሮች በመስጠት ለህዝብና መንግሥት የሚጠቅም ሥራ እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ  የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማኔጅንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ኤልያስ ገበየሁ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ ትኩረት አድርጎ ከሚሠራቸው ሥራዎች አንዱ በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ የተለያዩ ሥልጠናዎችን መስጠት ሲሆን በዚህም መሠረት ምርትና ምርታማነትን መጨመር የሚያስችል የ“Decision Support System for Agro-technology Transfer/DSSAT” ሞዴሎችና ሶፍትዌሮች ዙሪያ ለዞኑ ግብርና በላሙያዎች ሥልጠና ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ኤልያስ  በዓለማችን ከ87 በላይ ሀገራት፣  ከ25 ሺህ በላይ ተመራማሪዎች፣ ተማሪዎችና ፖሊሲ አውጭዎች ሶፍትዌሮቹን በመጠቀም ውጤታማ ሆነዋል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ መ/ርት ፍቅርተ ስዩም እንደገለጹት አሁን ባለንበት ሁኔታ በዓለም ላይ ከፍተኛ የምርት እጥረት ያለ በመሆኑ ያሉንን የእርሻ መሬትና የውኃ ውስን ሀብቶችን በዘመናዊ መንገድ በመጠቀም የተሻለ ምርት እንዲመረት በማድረግ እንደ ሀገር የሚታየውን የምግብ እጥረት ችግር ለመቅረፍ ታልሞ የሚሰጥ ሥልጠና ነው፡፡

የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሜቲዎሮሎጂና ሃይድሮሎጂ እና የውኃ ሀብትና መስኖ ምኅንድስና ፋከልቲዎች አሠልጣኝ መምህራን መ/ር ነብዩ ኦሊ እና  መ/ር ጌታቸው ኢንሳ በጋራ እንደገለጹት ‹‹Decision Support System for Agro-technology Transfer/DSSAT›› በሚል ርዕስ የሰጡት ሥልጠና በውስጡ ከ42 በላይ ሶፍትዌሮችን የያዘ ሲሆን ሶፍትዌሮቹ እያንዳንዳቸው የተለያዩ ተግባራት ያሏቸውና ባለሙያው በቢሮ ተቀምጦ ስለአንድ አካባቢ አየር፣ አፈርና ውኃ ሁኔታ ዳታ በመሰብሰብና በመተንተን ሞዴሎችን በመሥራት ሰብሎች ከመነሻ ጀምሮ እስከ ምርት መሰብሰቢያ ደረጃ ድረስ ምን ያህል ውኃ በምን ያህል ሄክታር እንደሚፈልጉ፣ የሚስማማቸውን የአፈር ዓይነትና የሚገኘውን የምርት መጠን በማወቅ አርሶ አደሮችን የማስተማርና ሥራቸውን በመደገፍ  የምርት መጠን ቀድሞ ከነበረው እንዲጨምር ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው፡፡

አቶ ደጀኔ ሙሉጌታ የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ባለሙያና ሠልጣኝ ስለሥልጠናው በሰጠው አስተያየት ሥልጠናው ማንኛውም የግብርና ባለሙያ የሆነ ሰው መሠልጠን የሚገባውና እንደ ሀገር የያዝነውን ግብርና መር ኢኮኖሚ እንዴት ማስቀጠል እንዳለብን መወሰን እንድንችል የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡     

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት