የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ከድሪም ፎር ዴቨሎፕመንት ድርጅት/Dream for Development International Ethiopia/ እና ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር ‹‹ምርጫ ለሀገር ህልውና ግዴታ ነው ወይስ አይደለም?›› በሚል ርእስ ግንቦት 22/2016 ዓ/ም በት/ቤቱ ተማሪዎች መካከል ክርክር አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የድሪም ፎር ዴቨሎፕመንት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሣሁን አሰፋ ድርጅታቸው በዋናነት የወጣቶች፣ ሕፃናትና ሴቶች እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን ንቃተ ህሊና በማሳደግ በሀገራቸው ዲሞክራሲያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የተሻለ ግንዛቤ ኖሯቸው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚሠራ ሀገር በቀል ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የክርክር መድረኩ የነገዋን ኢትዮጵያ የተሻለች ለማድረግ ታልሞ መዘጋጀቱን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አለመግባባቶችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲፈጠሩ ምርጫ አስፈላጊ መሆኑን እንዲሁም ከዚህ በተቃራኒ ከቀረቡ ሃሳቦችም አስተማሪ ጉዳዮችን ያየንበት ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የሲቪክ ማኅበራትና ድርጅቶች ክፍል አስተባባሪ አቶ ጥላሁን ሻንቆ መሰል መድረኮችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከተማሪዎችና ከተለያዩ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ጋር በማዘጋጀት በዲሞክራሲና በምርጫ ዙሪያ እንዲከራከሩና እሳቤ በመለዋወጥ ግንዛቤያቸውን እንዲያሳድጉ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በማኅበረሰቡ መካከል የሚፈጠሩ የተለያዩ አመለካከቶችን በማምጣት ማሰብ፣ መከራከርና መመካከር እንዲሁም በሃሳብ የበላይነት ማመን ተገቢ መሆኑን አቶ ጥላሁን አውስተዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት መምህራንና የክርክሩ ዳኞች ትምህርት ቤቱ መሰል የክርክር መድረኮችን በተለያዩ ጊዜያት ሲያቀርብ እንደነበር አስታውሰው ተከራካሪ ተማሪዎች ልምድ ያላቸው በመሆኑ ጠንካራና ገዥ ሃሳቦችን ማቅረባቸውንና በዳኝነት መስፈርቱ መሠረት በተያዘው ነጥብ አሸናፊውን መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት ምርጫ ለሀገር ህልውና ግዴታ ነው ያለው ቡድን 93.8 በማምጣት አሸናፊ ሆኖ 10 ሺህ ሲሸለም በተቃራኒው የቀረበው ቡድን 89.8 በማምጣት አምስት ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት የምርጫ መኖር ለሀገር ያለውን ፋይዳ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬታማ ከሆኑ ሀገራት ተሞክሮ እንዲሁም በተቃራኒው ከምርጫ ውጪ ዜጎቻቸው ስኬታማና ደስተኛ ሆነው የሚኖሩባቸውን ሀገራት ማየት የቻልንበትና ጥሩ ግንዛቤ ያገኘንበት ነው ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት