የግንቦት 20 ሃያ አራተኛ አመት የድል በዓል በዋናው ግቢ ግንቦት 26/2007 .ከብተና ስጋት ወደ ለዉጥ አብነት የተሸጋገረች ሀገር - ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በድምቀት ተከበረ፡፡

የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ በቀለ የግንቦት 20 ፍሬዎችን በተመለከተ ዘርዘር ያለና ሁሉንም ዘርፎች የዳሰሰ የመወያያ ሰነድ ለታዳሚዎች አቅርበዉ ጠለቅ ያለ ዉይይት ተደርጎበታል፡፡በሰነዱ ከግንቦት 20 ድል በኋላ በሀገራችን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ፣በመሰረተ ልማት ፣ በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና በሰላምና የውጭ ግንኙነት ዘርፎች የተመዘገቡ ድሎች ተዳስሰዋል፡፡

ሰነዱን መሰረት በማድረግ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ከግንቦት 20 ድል ወዲህ በሀገሪቱ የብሄር፣ የቋንቋ ፣ የባህል፣ የጾታ እና የሃይማኖት ነፃነቶች የተከበሩ ሲሆን በኢኮኖሚ ዕድገት ረገድም አለም ባንክና ሌሎች አለም-አቀፋዊ ተቋማት የመሰከሩለት እድገት የተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዉ እኛም የአይን እማኞች ነን ብለዋል፡፡በተለይም በትምህርትና በጤና ተቋማት ግንባታና ተደራሽነት እንዲሁም በመንገድ ግንባታ፣በቴሌኮሙኒኬሽንና በመብራት ኃይል አቅርቦት የተመዘገቡ ለዉጦች ለሌሎች ሀገራትም ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አስተያየት ሰጪዎች የተጀመረዉን የህዳሴ ጉዞ ማስቀጠል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በበአሉ አከባበር ስነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ እንደገለፁት ግንቦት 20 ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን አንድ የጨለማ ምዕራፍ ተዘግቶ ሌላ አዲስ ብርሃን ፈንጣቂ ምዕራፍ የተጀመረበት ነዉ፡፡በመሆኑም የሀገራችን ህዝቦች በሽምቅ ውጊያ፣በግድያ፣በአፈናና ዉምብድና ከመሰቃየት ወጥተዉ ወደ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ተሸጋግረዋል፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸዉ የትግሉ ሰማዕታት የህዝብን አጀንዳ አንግበው ወደ ትግሉ ሲገቡ ለራሳቸው እንደማያልፍላቸውና የህይወት መስዋዕትነት ሊከፍሉ እንደሚችሉ ቢያውቁም ለመጪው ትውልድ ብርሃንን ይፈነጥቁ ዘንድ ተሰውተዋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም የዛሬዉ ትዉልድ የህዳሴ ጎዳና ላይ ያለች ሰላማዊ ሀገር በመረከቡ ዕድለኛ ስለሆነ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሁሉ በአግባቡ በመወጣት ሀገራችን እየተገበረች ለምትገኘዉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የጀርባ አጥንት መሆን አለበት ሲሉም ተደምጠዋል፡፡በመጨረሻም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሀገራችን ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገዉን ሽግግር በመማር-ማስተማር፣በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ከወትሮዉ በበለጠ እንዲደግፍ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲዉ ከፍተኛ አመራሮች፣የአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች፣መምህራንና ተማሪዎች በበአሉ ላይ የተገኙ ሲሆን የጋሞ ጎፋ ዞን ባህላዊ ኪነት ባንድ የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችን በማሰማት በአሉን አድምቋል፡፡