በኮምፒዉተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከ1-4ኛ አመት ድረስ በሚማሩ ተማሪዎች የተሰሩ 16 አዳዲስ የኮምፒዉተር ፕሮግራሞች በዋናዉ ግቢ እና በአባያ ግቢ ከግንቦት 11-12/2007 .ም ድረስ ለዕይታ ቀርበዋል፡፡

በዓውደ ርዕዩ ለዕይታ ከቀረቡ የኮምፒዉተር ፕሮግራሞች መካከል የዉጪ ሀገርና የሀገር ዉስጥ ጎቢኚዎች ባሉበት ሆነዉ በኢንተርኔት አማካኝነት ሆቴል ለመያዝ፣የአዉቶብስ ቲኬት ለመቁረጥ ፣ ስለቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች መረጃ ማግኘት የሚያስችላቸዉና በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተማሪዎች መመረቂያ ጽሁፎች ዝግጅት ወቅት የሚከሰቱ ኩረጃዎችን ለመቆጣጠር የሚያግዙ ፕሮግራሞች ተጠቃሾች ናቸዉ፡፡

የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ኤግዚብሽኑን በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት በኤግዚብሽኑ የቀረቡት የኮምፒዉተር ፕሮግራሞች ችግር ፈቺ ከመሆናቸዉ በተጨማሪ በተማሪዎች የግል ጥረት መሰራታቸዉ የሚበረታታ ነዉ፡፡ ዶ/ር ፈለቀ አክለዉ ተማሪዎች እንዲህ አይነት ሥራ መስራታቸዉ ከበስተጀርባቸዉ ጠንካራ መምህራን መኖራቸዉንና የዩኒቨርሲቲዉን የትምህርት አሰጣጥ ጥራት የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸዉ በኤግዚብሽኑ የቀረቡት የፈጠራ ሥራዎች ዓለም በኮምፒዉተር ዕዉቀት የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ከምናከናዉናቸዉ ተግባራት አንዱ አካል መሆኑን ጠቅሰዉ የፈጠራ ሥራዎቹ ወደ ተግባር ሊለወጡ የሚችሉ ናቸዉ ብለዋል፡፡

በአዉደ ርዕዩ ወቅት በተሳታፊዎች በተሰጠዉ ድምጽ አሸናፊ የሆነዉ በተማሪዎች መመረቂያ ጽሁፎች ዝግጅት ወቅት የሚከሰቱ ኩረጃዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ፕሮግራም በመስራት ለዕይታ ያቀረበዉ-4ኛ አመት ተመራቂ ተማሪ አቤል ተመስገን ነዉ፡፡ተማሪ አቤል እነደተናገረዉ ተመራቂ ተማሪዎች መመረቂያ ጽሁፎቻቸዉን በሚያቀርቡበት ወቅት በፊት የተመረቁ ተማሪዎች ከሰሯቸዉ ሥራዎች በተወሰነ መልኩ ኮርጀዉ ስለሚያቀርቡ በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪዎች የተሰሩ ፕሮጀክቶች አንዳንዶቹ ተመሳሳይነት ይታይባቸዋል፡፡ ስለዚህ እሱ የሰራዉ የኮምፒዉተር ፕሮግራም በኢኒስቲትዩቱ የተሰሩ ፕሮጀክቶችን በጠቅላላ መዝግቦ መያዝ ስለሚያስችል ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ሲመጡ በቀላሉ ለይቶ ያሳዉቃል፡፡ኩረጃ በአንድ የኒቨርሲቲ ብቻ የማይወሰን አለም አቀፋዊ እና ሀገር አቀፋዊ ባህሪ ስላለዉ አሁን የሰራዉን ፕሮጀክት በዚህ ደረጃ የማሳደግ ህልም እንዳለዉም ተማሪ አቤል አስምሮበታል፡፡

በአዉደ ርዕዩ መዝጊያ ስነ-ስርአት ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲዉ መምህራን፣ተማሪዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በሰጡት አስተያየት እንዲህ አይነት አዉደ ርዕይ መካሄዱ ሌሎችንም ተማሪዎች የሚያነሳሳ መሆኑን በመጥቀስ የአዉደርዕዩ አቅራቢ ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ትምህርት በተግባር አሳይተዋል ብለዋል፡፡