ዩኒቨርሲቲው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የአከዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ቢሮ እና የሥርዓተ-ፆታ ዳይሬክቶሬት ገልፀዋል፡፡

በትምህርት ተቋማትና በሴክተር መስሪያ ቤቶች አመራር የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ መንግስት በያዘው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሰረት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 7 % የነበረውን የሴት መምህራን ቁጥር በ5 ዓመት ውስጥ ወደ 36% ለማሳደግ ዕቅድ ይዟል ፡፡በዚህም መሰረት በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ውሳኔ በ2007 /ም ከየትምህርት ክፍሉ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የተመረቁ 34 ሴት ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው በመምህርነት በመቅጠር ዕቅዱን ለማሳካት እየሠራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ደርዛ ገልፀዋል ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የስርዓተ ፆታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሙኒት መኩሪያ በበኩላቸው መምህራኑ በቅድሚያ የህይወት ክህሎት ፣ የጥናትና ምርምር ስነ-ዘዴ፣ የስርዓተ ፆታ ምንነትና ፅንሰ ሃሳብ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል ፡፡ እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ በርካታ ሴት መምህራንን መቅጠር የተፈለገው በዩኒቨርሲቲው በመምህርነትና በአመራር ላይ በቂ ሴቶች ባለመኖራቸውና በቀጣይም የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማሳደግ ብሎም ሴት ተማሪዎችን እንዲያበረታቱ ለማድረግ ነው ፡፡በመሆኑም አዲስ ተቀጣሪ መምህራን ጠንክረው እንዲሰሩና ለሌሎችም ተምሳሌት እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡