በማህበራዊና ስነ-ሰብ ኮሌጅ 118 አባላትን ያቀፈ የህግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ማህበር ጥቅምት 19/2008 ዓ/ም ተመስርቷል፡፡
የማህበሩ አባል ተማሪ ምስጋና ሙባረክ እንደገለፀችው የማህበሩ ዓላማ የዩኒቨርሲቲውንና የአካባቢውን ህብረተሰብ የህግ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ነፃ የህግ ድጋፍ መስጠት፣ ህግን ባለማወቅ ከሚመጡ ችግሮች መጠበቅና ግጭቶችን ከፍርድ ቤት ይልቅ በአማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች እንዲፈቱ ማስተማርና መደገፍ ነው፡፡ በተጨማሪም የህግ ተማሪዎችን በተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎት በማሳተፍ በዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በተለይም በፆታ እኩልነት በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የቀሰሙትን ትምህርት በተግባር እንዲለማመዱና የህግ ግንዛቤያቸውን በማሳደግ በመልካም ስነ- ምግብር እንዲታነፁና የዩኒቨርሲቲውን ህግና ደንብ እንዲያከብሩ የሚደርግም ነው ፡፡
የህግ ትምህርት ክፍል ተጠሪ መ/ር ደረጀ ማሞ የማህበሩ መመስረት ተማሪዎች ራሳቸውን ችለው በማህበረሰብ አገልግሎት እንዲንቀሳቀሱና ዩኒቨርሲቲው በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጪ ተቋማት ጋር ግንኙነት እንዲመሠርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል ፡፡
የጋሞ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ በቀለ በሻ ከህግ ሙያ ጋር ተያይዞ ትልቅ ኃላፊነት ፣ጊዜና ቦታ ሰጥቶ የመልካም አስተዳደር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የበለጠ ከፋ እንዲል የህግ እውቀት ያላቸውን የሰው ኃይሎች  በብዛት ማፍራት ወሳኝነት እንዳለው ዓላማ አድርጎ እየሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል ፡፡ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጎለብት የህግ የበላይነት ሊከበር የሚገባ ሲሆን  እነዚህ የዛሬዎቹ ተማሪዎች በጋራ ሆነው በአጠቃላይ ሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ከታች ጀምሮ ያለው ሃይል  ርብርብ ሲያደርግ ነው ብለዋል ፡፡
ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት የህግ ት/ቤት ለማህበረሰቡ እያደረገው ያለው የነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎቶች፣ ሰዎች በቤታቸው ሆነው  በነፃ የህግ መንገድ የሬዲዮ ፕሮግራም ስለ ህግና ሰብዓዊ መብቶች  ምንነት እንዲረዱ የማድረጉ ተግባር የሚበረታታ እንደሆነና ተማሪዎቹ በማህበር መዋቀራቸው ይህንንና መሰል ተግባራቶችን በመወያየት የበለጠ እንዲሰሩ ያስችላቸዋል ሲሉ  ተናግረዋል ፡፡
በመጨረሻም ለማህበሩ መመስረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ መ/ራንና ተማሪዎች የማበረታቻ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡