አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሣውላ ካምፓስ ለመጀመሪያ ጊዜ በ'Adult Education & Community development'፣ 'Communication & Media Studies'፣ 'Logistics & Supply Chain Management' እና 'Finance & Economic Development' 191 ተማሪዎችን ተቀብሎ ህዳር 19/2008 ዓ.ም ማስተማር ጀምሯል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ እንደገለጹት ተቋሙ የመማር ማስተማር ሥራውን በማሳደግ፣ የሥልጠና ዘርፎቹን በማስፋፋት እና የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎትን በማጣመር አካባቢውን ብሎም ሀገሪቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ በማኅበራዊ ሣይንስ እንዲሁም በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ዘርፎች የተጀመሩትን ሥራዎች በማጠናከር በቀጣይ በምህንድስናና በሌሎች ዘርፎች የትምህርት ፕሮግራሞችን አጥንቶ ለመክፈት ግብረ-ኃይል ተቋቁሟል፡፡
ፕሬዝደንቱ ለተማሪዎቹ አቀባባል በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የካምፓሱ መከፈት የጋሞ እና የጎፋን ህዝብ እንዲሁም የአ/ምንጭ እና የሣውላ ከተሞችን ትሥሥር የሚያጠናክር ተምሳሌታዊ ተግባር በመሆኑ ህብረተሰቡ ዘላቂ ትኩረትና ድጋፉን ሊቸረው ይገባል ብለዋል፡፡ ተማሪዎቹም በቆይታቸው ለሚገጥሟቸው ችግሮች የጋራ መፍትሄ ለማበጀት እንዲቻል ጥያቄዎቻቸውን በሠላማዊ መንገድ ማቅረብና ተባባሪነትን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የደኢህዴን/ማ/ኮ/ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው መንግሥት ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማስፋፋት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የካምፓሱ መከፈትም የማስፋፊያ ሥራው አካል ሲሆን ይህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥርጭትን ፍትሃዊ ለማድረግ የተጣለውን ግብ ለማሳካት ይረዳል፡፡ የአካባቢውን የልማት እንቅስቃሴ በማነቃቃት፣ በማፋጠንና ሠፊ የሥራ ዕድልን በመፍጠር ረገድም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም ልጆቻቸው የትምህርት ዕድል ለማግኘት በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ሲጓዙ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳቶች ይጋለጡ ነበር፡፡ የካምፓሱ በአቅራቢያቸው መከፈትም ይህንን ችግር የሚቀርፍና ከስጋት የሚያድናቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎቹ ቆይታቸው ምቹና ሰላማዊ እንዲሆን እና ችግሮች ሲከሰቱ በወቅቱ መፍታት እንዲቻል በህክምና አሰጣጥ፣ በምግብ  አቅርቦት፣ በውሃና መብራት አገልግሎት እንዲሁም በፀጥታ እና ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ከከተማ አስተዳደሩ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት