ከኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር እና ከ CDC/Center for Disease Control and Prevention/ ጋር በመተባበር የሚሠራው የአርባ ምንጭ ሥነ-ህዝብና ጤና ልማት ማዕከል በ2008 ዓ.ም የሀገር ዓቀፉ INDEPTH አባል ሆኗል፡፡ አስተባባሪው አቶ በፈቃዱ ታሪኩ እንደገለጹት INDEPTH የዲሞግራፊክ ሰርቬይላንስ ሳይቶች የመሠረቱት ዓለም ዓቀፍ ትሥሥር ሲሆን በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በጎንደር፣ መቀሌ፣ ጅማ፣ ሐረር እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ተመሥርቷል፡፡ የዚህ ሀገር ዓቀፍ ትሥሥር አባል መሆን የመረጃ ጥራትን ለማስጠበቅ፣ መሠረታዊ መረጃዎችን በINDEPTH ገጽ ለማስቀመጥ፣ የተለያዩ የጥናት ውጤቶችን በዓለም ዓቀፍ ጆርናሎች ለማሳተም እንዲሁም ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን ለማግኘት ዕድል ይፈጥራል፡፡
ማዕከሉ ተከታታይነት ያላቸው ማኅበረሰብን መሠረት ያደረጉ የስነ ህዝብ ጤና መረጃዎችን ማቅረብ፣ በሚቀርቡ መረጃዎች የህብረተሰቡን ጤና መከታተል፣ ለተመራማሪዎች ወቅቱን የጠበቀ ናሙና ማቅረብ፣ ለጤና ተመራማሪዎች የመስክ ላቦራቶሪ መሆን እና ለፖሊሲና ዕቅድ አውጭዎች ግብዓት መስጠትን ዓላማ አድርጎ በ2001 ዓ.ም በፕሮግራም ደረጃ ተቋቁሟል፡፡
በቅርቡ ወደ ማዕከልነት የተሸጋገረ ሲሆን በአ/ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በተመረጡ 9 ቀበሌያት ተከታታይነት ያላቸው የሞት፣ የውልደት፣ የጋብቻ ሁኔታ እና የአካባቢ ለውጥ መረጃዎችን በማሰባሰብ ለሚመለከታቸው አካላት ያደርሳል፡፡ የእናቶችና ህፃናት ጤና፣ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ ሥነ-ምግብ ዋስትና፣ የጤና ተቋም አጠቃቀምና መሰል ዋና ዋና የጤና ተጓዳኝ የህብረተሰብ ችግሮች ላይ የሚሰባሰቡ መረጃዎች የማዕከሉ ትኩረት ናቸው፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት