የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከኮምፒውተር ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ጋር በመተባበር ከአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢው 2ኛ ደ/መ/ት/ቤቶች ለተወጣጡ 95 መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ከታህሳስ 23 - ጥር 21/2008 ዓ/ም ለተከታታይ አራት ቅዳሜዎች መሠረታዊ የኮምፒውተር ክህሎት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ Click here to see the Pictures.

የኮምፒውተር ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ መሳይ ሳሙኤል  ከኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ካሜራዎች፣ ሪሞት ሴንሰሮች፣ ሮቦቶች፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮችና ኢንተርኔት መፈጠር ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፈጣን ዕድገት የተጫወተውን የላቀ ሚና በመጥቀስ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ፈጣንና  አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች የሚታዩበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የአካባቢው ህብረተሰብም የቴክኖሎጂው ተቋዳሽ እንዲሆን በMS-Word, MS-Excel, MS-Access, MS-PPT እና በኢንተርኔት አጠቃቀም ዙሪያ ስልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢው አልፎ በሌሎች የሀገሪቷ ማዕዘናትም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የክህሎት ውስንነት ለሚስተዋልባቸው ባለሙያዎች የአጭርና የረዥም ጊዜ ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የኮምፒውተር ክህሎት ስልጠና ሰልጣኞችን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማቀራረብ የኮምፒውተርና የመረጃ መረብ አጠቃቀም አቅማቸውን በማሳደግ ዕለታዊ ሥራዎችን እንዲያቀላጥፉ ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያበረክት ነው፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ ወልደመድህን ስልጠናው የተለያዩ አሰልጣኞችን በማፈራረቅ መሰጠቱ ተሞክሮዎችንና የስራ ላይ ልምዶችን ለመጋራት መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተሻለ ብቃት ያሳዩ ሰልጣኞች ተለይተው በዘርፉ ቀጣይ ስልጠናዎችን እንደሚያገኙም ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ የአሠልጣኞች ስልጠና በGIS እና GPS፣ በቴክኒካል ድሮዊንግና በcatia ሶፍትዌር አጠቃቀም ዙሪያ በዕቅዱ መሠረት የሚሰጥ ይሆናል፡፡

የጫሞ 2ኛ ደ/መ/ት/ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ወንድወሰን ጌታቸው ዩኒቨርሲቲው ላለፉት አራት ዓመታት የክህሎት ስልጠናዎች፣ የማጠናከሪያ ትምህርት ድጋፍ እንዲሁም የመምህራን እጥረት ሲያጋጥም አዎንታዊ ምላሾች በመስጠት የተለያዩ ቴክኒካዊ እገዛዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው በሙያው ዘርፍ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡ ለሠልጣኞች እና ለ22 የኮምፒውተር ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል አሠልጣኝ መምህራን በመድረኩ በተገኙ ኃላፊዎችና እንግዶች የምሥክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ እና ባዮሎጂ መምህራን በቤተ-ሙከራ አጠቃቀምና አያያዝ እና በሌሎች ዘርፎች የክህሎት ማጎልበቻ ስልጠናዎች በማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት እየተሰጠ መቆየቱ ይታወሳል፡፡