አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ነፃ የቀዶ ጥገና ህክምና አደረገ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች በገረሴ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለሚገኙ 10 ታካሚዎች ነፃ የቀዶ ጥገና ህክምና አገልግሎት ጥቅምት 23/2011 ዓ/ም ሰጥተዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የገረሴ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ስምዖን ሲዳሞ ዩኒቨርሲቲው ሆስፒታላችንን በተለያዩ መስኮች ለማገዝ ቃል በገባው መሠረት ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎችን በመላክ ይህንን ነፃ የቀዶ ጥገና አገልግሎት መስጠቱ ለባለሙያዎቻችን ልምድ እንዲያገኙ ከማድረጉ ባሻገር የታካሚዎችን ጊዜና ገንዘብ ከመቆጠብ አንፃር ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን ሁለተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም በአፅንዖት ጠይቀዋል፡፡

የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ወይንእሸት ገ/ፃዲቅ እንደገለፁት ሆስፒታሉ አዲስ የህክምና ተቋም እንደመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የባለሙያዎች ዕጥረት ያለበት መሆኑን ገልፀው ጽ/ቤታቸው ከሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቲው አካላት ጋር በመተባበር በተቋሙ የሚስተዋለውን የባለሙያም ሆነ የቁሳቁስ ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል፡፡ እንደ ኃላፊዋ ገለፃ ሌሎች ተመሳሳይ ከበድ ያሉ የቀዶ ጥገና አገልግሎትን በሆስፒታሉ ለማድረግ ያስችል ዘንድ ዩኒቨርሲቲው ከአንድ መቶ ሺ ብር በላይ ወጪ የቀዶ ጥገና ላቦራቶሪ ማሽን ለመግዛት የግዢ ሂደት ላይ ነው፡፡

የህክምና አገልግሎቱን የሰጡት ዶ/ር አለማየሁ ሻንቆ እና ዶ/ር አሸናፊ ነጋሽ በበኩላቸው የጀመሩትን ማህበረሰቡን በነፃ የማገልገል ሥራ በሌሎችም የህክምና ተቋማት በመገኘት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተው ሁሉም ሰው በየተማረበት መስክ ማህበረሰቡን የማገልገል ልምድን ሊያጎልብት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱን ያገኙ ታካሚዎች በበኩላቸው የተሰጣቸው አገልግሎት ሌላ ሆስፒታል ሄደው የሚያወጡትን ጊዜና ገንዘብ ማዳን እንደቻለ ገልፀው ለተሰጣቸው የህክምና ድጋፍ ለባለሙያዎቹና ለዩኒቨርሲቲው ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በአንድ ቀን የህክምና ውሎ 10 ታካሚዎች የቀዶ ጥገና ህክምና አገልግሎቱን ማግኘት ችለዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት