ዩኒቨርሲቲው የ2011 በጀት ዓመት የ3 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል አባላት በተገኙበት ጥቅምት 29/2011 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የስትራቴጂክ ዕ/ዝ/ት/ግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዝሙ ቀልቦ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተመለከተው የክረምት ተማሪዎች ቅበላምዝገባና፣ መማር ማስተማር ሥራ በተቀመጠው ጊዜ ሠሌዳ መሠረት መከነወኑ፣ አዳዲስ መጽሐፍት ወደ ላይብረሪ ሲስተም እንዲጫኑ መደረጉ2011 / የሚከፈቱ አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች በየደረጃው የማስገምገምና የማጽደቅ ሥራዎች መሰራታቸው፣ የPGDT ኮርስ ለ849 ሠልጣኞች በአግባቡ መሰጠቱ በአካዳሚክ ጉዳዮች ዘርፍ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡

በቴክኖሎጂ ሽግግር ወደ ማህበረሰቡ ለማሸጋገር በዕቅድ ከተያዙ 3 ቴክኖሎጂዎች ዉስጥ የወተት መናጫ የፕሮቶታይፕ ሥራዉ አልቆ ለማህበረሰቡ መሸጋገሩ፣ ለምርምር ሥራዎች ከዉጪ ድርጅት የ8 መቶ ሺ ብር ድጋፍ መገኘቱና ለፕሮጀክት ሥራ የሚሆን አንድ መኪና ድጋፍ ለማድረግ ውል መገባቱ፣ ሁለት ጤና ጣብያዎች 24 ሰዓትሶላር መብራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ፣ በነፃ የህግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ለ643 አቅመ-ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች ምክር፣ የክስ አቤቱታ ፅሁፍ ጥብቅና አገልግሎት መሰጠቱ፣ በላንቴ ክላስተር ለሚገኙ 1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለቤተ-ሙከራና ለቤተ-መጻህፍት አገልግሎት የሚውሉ በድምሩ 340 ወንበርና 100 ጠረጴዛ ድጋፍ መደረጉ፣ የቤሬ ተራራን መልሶ ለማልማት ከ4‚600 በላይ ችግኞች መተከላቸውና እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑ፣ 3 አዳዲስ የጎልማሶች ተግባር ተኮር ትምህርት ማስተማሪያ ማዕከላት መከፈታቸው በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ መልካም አፈፃፃሞች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የመምህራንና አስተዳደር ሠራተኞች ቅጥር በወቅቱ መፈጸሙ፣ የተማሪዎች ማደሪያ ዶርሞችና የኤሌክትሪክ መስመሮች ጥገና መከናወኑ፣ በአገራዊ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታ ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ የመምህራንና ሠራተኞች ውይይት መካሄዱ፣ የዩኒቨርሲቲ አከባቢ ማህበረሰብ ትስስር ፎረም አደረጃጀቶችን ለማጠናከር የጋራ ውይይት መደረጉ በሪፖርቱ የተካተቱ ሌሎች መልካም አፈፃፀሞች ናቸው፡፡

በሩብ ዓመቱ የካፒታል በጀት በወቅቱ አለመለቀቅ፣ ግዢዎች በተወሰነላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ከአቅራቢ ድርጅቶች ባለመድረሳቸው አገልግሎት ለማዳረስ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ፣ የተሸከርካሪ ዕጥረት መኖሩ፣ በተወሰኑ የሥራ ዘርፎች የሰዉ ኃይል(ባለሙያ) ዕጥረት መኖሩ በሩብ ዓመቱ የታዩ ችግሮች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

አፈፃፀም ግምገማው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮችና የኮሌጅ ዲኖች የተገኙ ሲሆን የተመዘገቡ መልካም አፈፃፀሞችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባና በሩብ ዓመቱ የታዩ ደካማ አፈፃፀሞች ላይ በመሥራት በቀጣይ ጊዜ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡