‹‹ከጎሳ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ እንስጥ!›› ‹‹ሁላችንም አብረን ነፃ ካልወጣን ማንም ብቻውን ነፃ ሊሆን አይችልም!›› በሚሉ መሠረታዊ መርሆዎች ላይ የሚሠራው የአዲሲቷ ኢትየጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተርና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ማኅበረሰብ ታኅሣሥ 13 እና 14 የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

ፕግራሙን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄረሰቦች አገር መሆኗን አስታውሰው ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች የአገራዊ አንድነትና የመቻቻል ባህላችን በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክሟል ብለዋል፡፡ እንደ ፕሬዝደንቱ ገለፃ ችግሩን ለመቅረፍ መሰል መድረኮች በተለይ የበርካታ ብሄረሰቦች መገኛ በሆኑት ዩኒቨርሲቲዎች የሚፈለገውን የሠላም፣ የአንድነትና የመቻቻል ባህል በማጎልበት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡

ከሰው ልጅ በላይ የሆነ ነገር ከፈጣሪ በስተቀር የለም ያሉት አቶ ኦባንግ ሁላችንም ከዘር፣ ከጎሳ፣ ከብሄርና እና ከምንከተለው እምነት በላይ ሰውነታችን ይበልጣል ብለዋል፡፡ አቶ ኦባንግ በንግግራቸው ማንም ሰው እናትና አባቱን፣ ጎሳውን፣ ብሄሩን፣ ፆታውን፣ የተወለደበትን ቦታና አገር፣ ነጭና ጥቁር መሆንን ፈልጎ እንዳልተወለደ ገልፀው ሰው ሆነን የተፈጠርነው ለእናትና ለአባታችን፣ ለብሄራችን፣ ለወረዳችን፣ ለዞናችን፣ ለክልላችን ብሎም ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለም ህዝብ በመሆኑ ለሁሉም ዜጎች ሰብዓዊ መብት መጠበቅ ኃላፊነት አለብን ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነገዪቱ ኢትዮጵያ ተስፋዎች እና መሪዎች መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት አቶ ኦባንግ ማንም ብሄር የማንም ጠላት አለመሆኑን፣ አብረዋቸው የሚማሩት ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው መሆናቸውንና ከምንም በላይ ሰው መሆናቸውን ተገንዝበው በፍቅር፣ በመቻቻልና በሠላም አብረው ሊማሩ ይገባል ብለዋል፡፡

ለአገራችን አንድነት መረጋገጥና ለሁላችንም እኩልነትና ሰብዓዊ መብት መጠበቅ አማራው፣ ኦሮሞው፣ ወላይታው፣ ጋሞው፣ ትግሬው፣ ሶማሌው ወዘተ በመካከበርና መቻቻል የመኖር ባህልን ማጠናከር አለበት ያሉት አቶ አቦንግ ተማሪዎችም ይህንን ተረድተው የሚማሩት አስቀድመው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ለመቀየር ሲሆን ሲቀጥልም የአከባቢያቸውንና የአገራቸውን ሕዝብ ሕይወትና ኑሮ ለማሻሻልና ከሁሉም በላይ የሁሉንም ሰው ዘር ልጆች በሰብዓዊነትና በቅንነት ለማገልገል ነው ብለዋል፡፡

‹‹እኔ አኝዋክ ነኝ፤ በአኝዋክነቴ እኮራለሁ፤ ነገር ግን አኝዋክነቴ ከሰውነቴ አይበልጠብኝም!›› ያሉት አቶ ኦባንግ ከምንም በላይ መቅደም ያለበት ሰው መሆናችን ነው እንጂ ጎሳችን ወይም ብሄራችን መሆን የለበትም ብለዋል፡፡  አቶ ኦባንግ አሁን ላይ በአገራችን ብሎም በዩኒቨርሲቲዎች ብሄርን መሠረት በማድረግ እየተነሱ ላሉ ግጭቶች ተጠያቂዎቹ ለበርካታ ዓመታት ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፣ ከአንድነት ይልቅ መለያየትን ሲዘሩ የቆዩት ፖለቲከኞች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ብሄርተኝነት እንደ ኒውክሌር ቦንብ አገርን ሊያጠፋ የሚችል አደጋ ያለው በመሆኑ በሩዋንዳና ዩጎዝላቪያ ሕዝቦች ታሪክ በመማር ፖለቲካውን የሚመሩ አካላትና ፖለቲከኞች  ከብሄር ይልቅ በአስተሳሰብ ወይም በርዕዮተዓለም መደራጀት የሚችሉበት ድርጅታዊ የሕግ የአደረጃጀት ማዕቀፍም ሊታሰብ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡

በመድረኩ በርካታ ወቅታዊና አገራዊ እንድምታ ያላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተማሪዎች፣ ከመምህራንና ሌሎች ተሳታፊዎች ቀርበው በአቶ ኦባንግ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት