በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አገራዊው የጽዳት ዘመቻ ተካሄደ

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጥሪ መሠረት‹‹አካባበቢያችንን እናፅዳ ጤናችንን እንጠብቅ፤ ሠላማችንን እናስፋ!›› በሚል መሪ ቃል ሚያዝያ 06/2011 ዓ/ም በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የጽዳት ዘመቻ ላይ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በንቃት ተሳታፊ ሆኗል፡፡ በፅዳት ዘመቻው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲውን ቅጥር ግቢና ከተማውን በማጽዳት ተሳትፈዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ባስተላለፉት መልዕክት በአገሪቱ  የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሰባሰቡ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሠራተኞች የሚገኙባቸው መሆኑን አስታውሰው ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ለሀገርና ለህዝቦች አንድነት በአርኣያነት እንዲቆምና እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡
ዛሬ ከአካባቢያችን ቆሻሻን በማጽዳት እንዳስዋብነው ሁሉ ከአዕምሮችን ዘረኝነትን፣ ጥላቻንና መጥፎ ሃሳብን በማስውገድ በሀገራችን አሁን ላይ እየታየ ያለውን የእርሰ በእርስ ግጭትና መፈናቀል እንዲጠፋ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲውና በከተማው  በተካሄደው የጽዳት ዘመቻ ተሳታፊ  መምህራን፣ ሠራተኞችና ተማሪዎች እንደገለፁት ቆሻሻ የማጽዳት ሥራው  ዓላማ ዩኒቨርሲቲውንና ከተማዋን ለኑሮ የተመቸች፣ ንፁህ፣ ውብና ማራኪ  እንዲሁም ለጤና ተስማሚ እንድትሆን ለማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ዘርን መሠረት ያደረጉ የጥላቻ አመለካከቶችንና በኢትዮጵያዊ አንድነትና በቆየ የአብሮነት ባህል ላይ የተጋረጡ እንቅፋቶችን ከሥራቸው ከመንቀል አንጻር ትልቅ እንድምታ ያለው በመሆኑ በታላቅ ተነሳሽነት በዘመቻው ተሳትፈዋል፡፡
እንደ ዘመቻው ተሳታፊዎች መልዕክት ዩኒቨርሲቲዎች  ኢትዮጵያዊነት በጉልህ ከሚንፀባረቅባቸው ተቋማት መካከል ግንባር ቀደም ከመሆናቸውም ባሻገር ኢትዮጵያዊያን ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምስራቅና  ምዕራብ ጫፎች የሚሰባሰቡበትና ተቻችለው የሚኖሩበት እንደመሆኑ መሰል ተግባራትን በማከናወን ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ወደምትታወቅበትና ወደ ነበረችበት ታላቅነት፣ አንድነትና የአብሮነት ባህል ለመመለስ መሰል ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት