የዩኒቨርሲቲው BENEFIT-REALISE (ቤኔፊት ሪያላይዝ) ፕሮግራም ከደራሼ፣ ምዕራብ አባያ፣ ዛላና ቁጫ ወረዳዎች  ለተወጣጡ 44 የወረዳ የግብርና ሰብልና አግሮኖሚ ባለሙያዎች፣ የፅ/ቤት ኃላፊዎች እና የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ከነሀሴ 15 – 17/2011 ዓ/ም ድረስ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ


ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጉ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር መልካሙ ማዳ ግብርና ላይ ትኩረት በመስጠት ምርትና ምርታማነት እንዲያድግና የአርሶ አደሩ ኑሮ እንዲሻሻል የግብርና ባለሙያዎች  የበኩላቸውን ግዴታ በመወጣት ለውጤቱ በጋራ መረባረብ አለባቸው ብለዋል፡፡  ሰልጣኞች ከስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በትክክል ተገንዝበው ለአርሶ አደሩ ማስተላለፍና መደገፍ እንዳለባቸውና ያጋጠሙ ችግሮችንም በመለየት በቀጣይ የሚሻሻልበት መንገድ ላይ በጋራ ሊመክሩ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡  
የቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ የስልጠናው መሠረታዊ ዓላማ የባለሙያዎችን አቅም በማጎልበትና ምርትና ምርታማነትን ከፍ በማድረግ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ አርሶ አደሮችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥና ገቢያቸውን  ማሳደግ ነው፡፡ እንደ አስተባባሪው በተጨማሪም በበልግ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን በመቅረፍ  ለመኸር ወቅት ከሚቀርቡ የጓሮ አትክልቶች  ጋር ተያይዞ  በአዘራር፣ በግብዓት አጨማመርና በሽታ መከላከል ዙሪያ ያላቸውን  ግንዛቤ ማዳበር ነው ብለዋል፡፡  
እንደ ዶ/ር መብራቱ ገለፃ  በየአካባቢው በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የግብአት መቅረብ፣ በዕፅዋት በሽታ መከላከልና ተዛማጅ ጉዳዮችን እንደታቀደው መስራት ባይቻልም ችግሮችን በማለፍ ስራዎችን በጥሩ ሁኔታ ማከናወን ተችሏል ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት በአርሶ አደሮች የተለዩ ምርጥ ዝርያዎች ከበቆሎ BH547፣ ከማሽላ ‹‹መልካም›› ፣ ከድቡልቡል ድንች ‹‹በለጠ›› እንዲሁም ሌሎች የቦለቄ ዝርያዎችን የማሰራጨት ስራ በቀጣይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
አርሶ አደሩ ገበያ መር የሰብል ዓይነቶችን እንዲያመርትና  የገበያ ትስስርን መፍጠር እንዲችል ለማድረግ የባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ያሉት ዶ/ር መብራቱ  አርሶ አደሩ  ማምረት ብቻ ሳይሆን ገበያ ላይ ተፈላጊነትና ዕጥረት የሚታይባቸውን ምርቶች በመለየትና ዕሴት በመጨመር ትስስሩን ባማከለ መልኩ ወደ ምርት እንዲመጣ ማስቻል ይገባል ብለዋል፡፡
በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የእጽዋት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መ/ር ረ/ፕ ቢተውልኝ እሸቱ  የጓሮ አትክልት አመራረት ሂደትን ከማሳና ዘር ዝግጅት ምርትን ለገበያ እስከ ማቅረብ ያለውን ሂደት በሳይንሳዊ መንገድ በስልጠናቸው  ቃኝተዋል፡፡ እንደ አሰልጣኙ ገለፃ ቀይ ሥር፣ ካሮት፣ ጥቅል ጎመን፣ ደንቀሌ፣ ስኳር ድንች፣ ፓፓያ፣ ሰላጣና ቆስጣ በአጭር ጊዜ የሚደርሱና ማንኛውም ሰው ሊዘራቸው የሚችላቸው፣ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸውና አጥጋቢ ምርት የሚሰጡ በመሆናቸው  አርሶ አደሩ ድቃይ ዝርያዎችን በመጠቀም የጓሮ አትክልቶችን በደንብ እንዲያመርትና የራሱን የምግብ ዋስትና እንዲያስጠብቅ ብሎም  ለገበያ ሲወጣም በአቅራቢያው ያለው ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስተማር ይገባል ብለዋል፡፡ አክለውም አርሶ አደሩ በሽታዎች ሲከሰቱ የተለያዩ  መድኃኒቶችን በግምት በመጠቀም በርካታ ወጪ ከሚያወጣ ባለሙያዎችን ቢያማክር የተሻለ ነው ብለዋል፡፡
ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው እጅግ ጠቃሚና ለመኸር ሥራ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረው በፕሮግራሙ በመታቀፋቸው ዕድለኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል የዘር አቅርቦት መዘግየት እየተስተዋለ በመሆኑ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
ስልጠናው በግብርና ኤክስቴንሽንና ኮሚዩኒኬሽን፣ በሰርቶ ማሳያ፣ በ PBS፣ በዕቅድ ዝግጅትና በመረጃ አያያዝ በሚሉ ይዘቶች ዙሪያ የተሰጠ ሲሆን የወረዳዎች የሥራ አፈፃፀም ሪፖርትም ቀርቦ ግምገማና አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት