አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 2ኛውን ‹‹የአረንጓዴ አሻራ ቀን›› ከአርባ ምንጭ ከተማና ከጋሞ ዞን አመራሮች ጋር በመሆን ከሁለት ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል ግንቦት 28/2012 ዓ/ም በይፋ አስጀምሯል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በ2011 ዓ/ም ክረምት በተደረገው የመጀመሪያው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በስፋት መሳተፉንና በወቅቱ ከተተከሉ ችግኞች መካከል 94 በመቶ ያህሉ መፅደቃቸውን አስታውሰዋል፡፡Click her to see the pictures

 

በዘንደሮ ክረምትም ከአምናው በተሻለ ሁኔታ በርካታ ችግኞችን ለመትከል ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ክረምቱን ሙሉ በሚደረገው የችግኝ ተከላ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ራሱን ከኮሮናቫይረስ እየጠበቀና ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ በመርሃ-ግብሮቹ ላይ በንቃት በመሳተፍ  የበኩሉን ሚና እንዲወጣ  ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ47ኛ በሃገር ደረጃ ለ27ኛ ጊዜ በደቡብ ክልል የተከበረውን የዓለም አከባቢ ቀንን ምክንያት በማድረግ ዩኒቨርሲቲው የ2012 ዓ/ም «የአረንጓዴ አሻራ›› መርሃ-ግብር በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ʻኮቪድ-19 እና አከባቢʼ በሚል መሪ ቃል በይፋ የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት አዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
በዚህ ክረምት ዩኒቨርሲቲው ከ50 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ቅደመ ዝግጅት ማድረጉን የገለፁት ዶ/ር ስምዖን በዛሬው መርሃ-ግብርም ከሴቻ አጂፕ ጀምሮ ወደ ኮንሶ መውጫ ዋና መንገድ ግራ፣ ቀኝና መኃል ይዞ እስከ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ድረስ፣ በኢትዮ-ፊሸሪ የጋራ መኖሪያ አከባቢዎች እንዲሁም በኩልፎና አባያ ካምፓሶች በአጠቃላይ ከሁለት ሺህ በላይ ልዩ ልዩ ዝርያ ያላቸው ለምግብነት፣ ለጥላና ለውበት የሚሆኑ ችግኞች መተከላቸውን ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡
የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው  ለ2ኛ ጊዜ በሚካሄደው ‹‹የአረንጓዴ አሻራ›› መርሃ-ግብር ዩኒቨርሲቲው በሰባት ወረዳዎች ባሉት ዘጠኝ ችግኝ ጣቢያዎች ከ100 ሺህ በላይ የተለያዩ ችግኞችን ማዘጋጀቱን ገልፀው 50 ሺህ ያህሉ በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የሚተከል ሲሆን ቀሪው ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚከፋፈል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ተክሉ ገለፃ በዘንድሮው የክረምት መርሃ-ግብር ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ እንደ ከዚህ ቀደሙ ማኅበረሰቡን ባንድ ላይ መሰብሰብ ስለማይቻል ተራ በተራ እየተወጣና አስፈላጊው  ጥንቃቄ እየተደረገ  ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ ይሠራል፡፡
የዕለቱ ተከላ ተሳታፊዎች የፊት መሸፈኛ ጭንብሎችን በማድረግና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ተከላውን ያከናወኑ ሲሆን በቀጣይም ክረምቱን ሙሉ በሚኖሩ የተከላ ፕሮግራሞች በተመሳሳይ ሁኔታ የኮሮናቫይረስ መከላከል ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ ይሆናል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት