አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2012 የአረንጓዴ አሻራ ቀንን አስመልክቶ ለ2ኛ ጊዜ በስድስቱም የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶችና በቤሬ ተራራ ላይ ዛሬ ሰኔ 8/2012 ዓ/ም የችግኝ ተከላ አካሂዷል፡፡ምስሉን ለመመልክት ከዚህ ይጫኑ


በችግኝ ተከላው ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና አስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚገኙ የኢንተርን ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በዛሬው ዕለት ብቻ 5,521 ችግኞች ተተክለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለፁት የ2012 የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በዩኒቨርሲቲው ግንቦት 28/2012 ዓ/ም መጀመሩን አስታውሰው ተግባሩም ክረምቱን ሙሉ የሚቀጥል ነው ብለዋል፡፡ የዛሬው ተከላ እንደ ሀገር የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተከላ እንዲያከናውኑ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የተፈጸመ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ችግኞችን ከመትከል ባሻገር የመንከባከብና የመከታተል ሥራ ወሳኝ መሆኑን ያወሱት ፕሬዝደንቱ የተተከሉት ችግኞች ሙሉ በሙሉ እንዲጸድቁ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው በትኩረት ይሠራል፡፡ ሥራውንም በዋናናት የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በባለቤትነት የሚመራው መሆኑንም ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል፡፡
የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው በዛሬው ዕለት በነበረው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የነበረው የማኅበረሰቡ ተሳትፎ አበረታች መሆኑን ጠቁመው ተሳትፎው ክረምቱን ሙሉ በሚኖረው የተከላ መርሃ ግብሮችም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡ በዛሬው መርሃ ግብር 5,521 ችግኞች የተተከሉ ሲሆን ይህም ከዕቀድ አንፃር 92 በመቶ መሆኑን ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በሁለት ዙር ባደረገው የችግኝ ተከላ 8,750 ችግኞችን የተከለ ሲሆን በክረምቱ እስከ 50 ሺህ ችግኞችን ለመትከል አቅዶ እየሠራ ይገኛል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት