ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ (Geological survey of Ethiopia) ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችለውንና ለ5 ዓመታት የሚቆይ የጋራ ስምምነት ውል መጋቢት 27/2013 ዓ/ም ተፈራርሟል::

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ኢንደስትሪዎች ለሀገራቸው ልማት በትስስር መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረው ከሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ጀምሮ ተማሪዎችን በመቀበል ሂደትና በሥልጠናዎች እየተናበቡ ለመሥራት በ10 ዓመት ዕቅድ ላይ የተቀመጠ ነው ብለዋል፡፡ በስምምነቱ መሠረት በዝርዝር በተቀመጡ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ የእናትፋንታ መላኩ እንደገለጹት ተጠሪነቱ ለማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የሆነው ተቋማቸው ለኢትዮጵያ ጂኦ ሳይንስ ተቋም መረጃን በመሰብሰብና በመተንተን ለሀገሪቱ የሥነ-ምድር ጥናት መረጃዎችን የሚያዘጋጅ ሲሆን ከማዕድን ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሥራዎችንም ይሠራል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ ተቋሙ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተፈራረመው ስምምነት መሠረት በዋናነት ጥናትና ምርምሮችን መሥራት፣ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በተቋሙ የተግባር ልምምድ እንዲያገኙ ማመቻቸት እንዲሁም የማዕድን ጥናቶችንና የቤተ-ሙከራ ሥራዎችን የሚሠራ ይሆናል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከተቋሙ ጋር የማዕድን ጥናትና ሌሎች ሥራዎችን ሲሠራ እንደነበር አስታውሰው የጋራ መግባቢያ ስምምነት መፈረሙ በምርምርና ሥልጠና ዘርፎች ይበልጥ በቅንጅት ለመሥራት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት፣ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ዋና ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት