የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲው ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ከሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ከ6ቱ ካምፓሶች የተለያዩ ሥራ ክፍሎች ለተወጣጡ አስተባባሪዎች፣ ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች ከየካቲት 01-02/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ በሥልጠናው የአእምሮ ዕውቀት፣ የስሜት ልህቀት፣ ስብእናና ተፈጥሯዊ ባህሪያት በስፋት ተዳሰዋል፡፡ 

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት ት/ክፍል የ2ኛ ዓመት ተማሪ የነበረችው ጽጌረዳ ግርማይ በቅርብ ጓደኛዋ ተማሪ በደረሰባት የስለት ጥቃት ጥር 23/2014 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷን አስመልክቶ በኮሌጁ አስተባባሪነት የካቲት 01/2014 ዓ/ም የሻማ ማብራት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ መንግሥት ፍትሕ ቢሮ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ጋር በመተባበር በፍትሐብሔር አሠራር ማኑዋል፣ በግንባታ ውሎች፣ በፍርድ ቤት ሥልጣን፣ በክስ አቀራረብና መስማት ሂደት እና በመጥሪያ አደራረስ ላይ በክልሉ ከሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ ዐቃቤያን ሕግ ከጥር 28-29/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ዲግሪ ነባር የክረምት መርሃ-ግብር ተማሪዎች ከየካቲት 14-19/2014 ዓ.ም ድረስ ቲቶሪያል የሚሰጥ ስለሆነ በየካምፓሶቻችሁ ተገኝታችሁ ገለጻውን እንድትከታተሉ ዩኒቨርሲቲው ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሕወሓት ወራሪ ኃይል ከፍተኛ ጉዳት ላጋጠመው ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ለመማር ማስተማር ሥራ የሚውሉ ላፕቶፖች፣ ወረቀቶች፣ ካኪ ፖስታዎች፣ እስክሪብቶዎች፣ ቾክ፣ የቢሮና የተማሪ ወንበሮች፣ የማስተማሪያ ጠረጴዛዎች፣ ለተማሪ የምግብ አገልግሎት የሚውሉ የካፍቴሪያ ዕቃዎች፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ፕላስቲክ ጋኖች፣ የእንጀራ ምጣዶች፣ የፍራሽ፣ የዕቃ ማመላለሻ ጋሪዎችና የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን ጥር 21 እና 22/2014 ዓ.ም በወልድያ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ድጋፍ አድርጓል፡፡ የቁሳቁስ ድጋፉ በገንዘብ ሲተመን 2.5 ሚሊየን ብር የሚያወጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡