የፎረሙ ውይይት በዋናው ግቢ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣የአስተዳደር ሠራተኞች፣ መምህራንና ተማሪዎች በተገኙበት ሚያዝያ 30 ተካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ኮንፈረንሱን በንግግር በከፈቱበት ወቅት መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል የትምህርት ጥራትና የመልካም አስተዳደር ፎረም ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የፎረሙ ተሳታፊዎች ከመልካም አስተዳደርና ከትምህርት ጥራት አንፃር መሻሻል የሚገባቸውን አፈጻጻሞች በተመለከተ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ በሚያስችል መልኩ ውይይቱን እንዲያካሂዱ አሳስበዋል፡፡

ኮንፈረንሱ በዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል በትምህርት ክፍሎችና በኮሌጆች ደረጃ በተከታታይ በተደረጉ ውይይቶች ተለይተው የወጡ ችግሮችንና ድክመቶችን እንደየባህሪያቸው የአጭር፣ የመካካለኛ እና የረዥም ጊዜ ዕቅድ በማውጣት በዘላቂነት ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ የሁሉንም ኮሌጆችና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ሪፖርቱን ተከትሎ የሁሉም ኮሌጆች ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች አስተያየቶችን፣ ጥቆማዎችንና ጥያቄዎችን በመሰንዘር የመብራት፣ የኢንተርኔት፣ የውሃና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶች አካባቢ የሚታዩትን ክፍተቶችና ከፍተኛ መሻሻሎች ገምግመዋል፡፡

ዲኖቹ ለአስተያየትና ጥቆማ ሰጪዎች ምስጋና በመቸር ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሠጡበት ወቅት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል መምህራን የትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ መደረጉን፣ የብቃት ችግር አለባቸው የተባሉ የአንዳንድ የውጭ አገር መምህራን ኮንትራት መቋረጡን እንዲሁም መምህራን የተማሪዎችን ፈተና በወቅቱ አርመው ውጤታቸውን የሚያሳዩበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ከትምህርት ክፍሎች ጋር በመተባበር እየተሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ የ1 5 አደረጃጀት በሁሉም ክፍሎች ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውን የሚያስችልና ክትትል የሚያደርግ ከአስተዳደር ሰራተኞች፣ ከመምህራንና ከተማሪዎች የተወከለ የሱፐርቪዢን ቡድን ተቋቁሞ ሥራ ላይ መሆኑንም አሳውቀዋል፡፡

የሁሉም ኮሌጆች ዲኖች እንደተናገሩት ከተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም ከአስተዳደር ሠራተኞች የስኬት ማነቆ ሆነው የተለዩትን ችግሮች ለመቅረፍ በተቀመጠው መርሃ ግብር መሠረት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ሊፈቱ የታቀዱ ችግሮችን በተቀናጀ ጥረት ለመሻገር በርትተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡

/ር ፈለቀ ኮንፈረንሱን ሲያጠቃልሉ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ሊተገበሩ የታቀዱ እንዲሁም እስከአሁን መፍትሔ ያልተሰጣቸው የተወሰኑ የአጭር ጊዜ ተግባራት በቀጣይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራባቸው በመግለጽ የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ የትምህርት ልማት ሠራዊት ግንባታን ይበልጥ በማጠናከር የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ ሁሉም ባለድርሻዎች በቅንጅት እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የግብርና ሣይንስ ኮሌጅ በስሩ በተከፈቱ 7 የትምህርት መስኮች ዘርፈ ብዙ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በእንስሳት፣ በእፅዋት እና ደን ሳይንስ የትምህት ዘርፎች የሚካሄዱት ምርምሮች ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የዕፅዋት ሣይንስ ትምህርት ክፍል ተጠሪ አቶ ኪያ አደሬ እንደገለጹት በትምህርት ክፍላቸው ጥራጥሬና ሰብሎችን አራርቆ መዝራት፣ ተፈጥሯዊና ዘመናዊ ማዳበሪያ አጠቃቀምን ጨምሮ የተለያየ እንክብካቤ በመስጠት የምርታማነት ዕድገትን ለመጨመር የሚያስችሉ ዘዴዎችን ለመለየት በትጋት እየተሰራ ነው፡፡

በዋናው ግቢ የእርሻ ምርምር ማሳያ ላይ እየተካሄደ ያለውን የሸንኮራ አገዳ ምርምር አስመልክተው ፕሮፌሰር አብዱል ቀይም ከሃን እንደተናገሩት ዩ ኤስ ኤን ጨምሮ ከተለያዩ 8 አገሮች የተሰባሰቡ 16 ዓይነት የሸንኮራ አገዳ ምርጥ ዝርያዎች እየተጠኑ ነው፡፡ ለወደፊትም ለኦሞ ኩራዝ፣ ለወንጂና ለመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች የተሻለ ግብዓት እንዲሆን ምርምሩን ስኬታማ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል፡፡

የደን ሣይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮናስ ኡጎ በበኩላቸው ትምህርት ክፍላቸው የአካባቢውን የደን ሀብት ለማሳደግ የሚያስችሉና ከአካባቢው የአየር ንብረት ጋር ተዛማጅ የሚሆኑ የዛፍ ዝርያዎችን በማጥናት ችግኝ አፍልቶ ለዩኒቨርሲቲው ካምፓሶችና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የማድረስ ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡ በዚህ ዓመት ከድሬዳዋ ተገዝቶ የመጣውን የእውነተኛ ኒም ዛፍ ችግኝ በማፍላት እስከ አሁን ከ14,000 በላይ ችግኞች የተሰራጩ ሲሆን በዘርፉ ቀጣይ ምርምሮችን በማካሄድ ከአንድ በላይ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ ዛፎችን ለማስተዋወቅና ለማላመድ አቅደን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የእንስሳት ሣይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ሠይፉ ብርሃኑ በትምህርት ክፍላቸው ምርጥ የወተት ላም ዝርያዎችን ከአካባቢው ዝርያዎች ጋር የማዳቀል ሥራ በቅርቡ የሚጀመር መሆኑን በመጥቀስ የእንስሳት መኖ ዕፅዋትን በማላመድ ለምርጥ የወተት ላሞችና ለዶሮ እርባታ ሥራዎች ግብዓት እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የፕሮፌሰር ሰለሞን ‘chicken brooding box’ የተባለ ዘመናዊ የጫጩት ማሳደጊያ አጠቃቀም ጥናት እንደተጠናቀቀም ቴክኖሎጂው ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ይሆናል፡፡

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ነጂብ መሐመድ እንደተናገሩት ኮሌጁ ከተቋቋመ ገና ሁለት ዓመት ብቻ ቢሆነውም እየሠራቸው ያሉት ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ ዲኑ በኮሌጁ ባሉት ሁሉም የትምህርት ክፍሎች በመምህራንና በተለይም በተመራቂ ተማሪዎች አበረታች ምርምሮች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልፀው የተጀመሩትና ሌሎችም አዳዲስ ምርምሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት በአባያ ክ/ከተማ በኩልፎ ቀበሌ ለተገኙ በርካታ አረጋዊያንና ወላጅ አጥ ሕፃናት የ2007 .ም የፋሲካ በዓልን በማስመልከት የምሳ ግብዣ አድርጓል፡፡

የሰጪ እጅ ሁሌም ከላይ ነው” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን የምሳ ግብዣ ያሰናዱት የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ጌትነት ዓለሙና የተማሪዎች ዲስፕሊን ተጠሪ ተማሪ ታመነ ዳኘው ናቸው፡፡ ተማሪ ጌትነት ባደረገው ንግግር የአ//ዩን ተማሪዎች ወክሎ ከታዳሚዎቹ መሃል በመገኘት በዓሉን ማክበሩ እንዳስደሰተውና ለወደፊትም በተመሳሳይ መልክና የበለጠ አቅም በመፍጠር በዓላትን በጋራ ለማሳለፍ እንደሚሠሩ ተናግሯል፡፡

በአባያ ክ ከተማ የኩልፎ ቀበሌ ወጣቶችና ስፖርት ዘርፍ ኃላፊ ወጣት ተክሌ ብርሃነገነት እና የአርባ ምንጭ ከተማ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽ ቤት ምኃላፊና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ ወጣት በላይ ግዛቸው የአዩ ተማሪዎች ኅብረት ያደረገውን ድጋፍ አመስግነው ለወደፊትም መሰል ትብብርና በጋራ የመሥራቱ ልምድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ በዝግጅቱ መጨረሻም የአ ዩ ተማሪዎች ኅብረት ለተሳታፊ ስፖንሰሮች የተሰጠውን የምሥክር ወረቀት ወስዷል፡፡

 

በተመሳሳይም የአ//ዩ ከፍተኛ የአስተዳደር አካላት በ5ቱም ካምፓሶች ከተማሪዎች ጋር በመሆን የፋሲካን በዓል በድምቀት አክብረዋል፡፡ በዋናው ግቢ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ከሌሎች የአስተዳደር አካላት፣ የተማሪዎች ፕሬዝደንትና የተማሪዎች ተወካይ ኮሚቴዎች ጋር በመገኘት በዓሉ ደማቅ እንዲሆንና ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳሉ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ድባብ ፈጥረዋል፡፡

በሌሎቹም ካምፓሶች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖችና የሥራ ክፍል ኃላፊዎች እንዲሁም የተማሪዎች ተወካዮች ከተማሪዎች ጋር በመሆን በዓሉ በልዩ ድምቀት እንዲከበር አድርገዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሰላም ፎረም ከግንቦት 22-23/2004 .ም በዋናው ግቢ በሰጠው ስልጠና በአምስቱም ግቢዎች የሚገኙ የተማሪዎች የሠላም ፎረም ፕሬዝደንቶችና አባል ተማሪዎች፣ አባል መምህራን፣ የካምፓስ አስተዳደሮች፣ የፀጥታና ደህንነት ሰራተኞች፣ዳይሬክተሮች፣ የጋሞ ጎፋ ዞን ፀጥታ አስተዳደር መምሪያ ተወካዮችና የሃይማኖት መሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ስልጠናውን በንግግር ሲከፍቱ እንደገለጹት ከዚህ በፊት ከአገልግሎት አሰጣጥና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች ግጭቶች ይነሱ እንደነበር በማስታወስ ይህ ፎረም ከተቋቋመ በኋላ ግን በርካታ ችግሮችን በመቅረፍ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

ከደቡብ ክልል ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ተወክለዉ የመጡት አሰልጣኝ አቶ ኃይሉ ማቲዮስ በበኩላቸው በክልላችን በሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ይህ መዋቅር አበረታች እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡አቶ ማቲዮስ አያይዘዉ አደረጃጀቱ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ከመውረዱ በፊት ባለማወቅ ችግር ይፈጥሩ የነበሩ አንዳንድ ተማሪዎች ከጥፋታቸው ሙሉ በሙሉ በመዉጣት የሰላም አምባሳደር እስከ መሆን ደርሰዋል ብለዋል፡፡

የስልጠናዉ ትኩረት አቅጣጫ በዩኒቨርሲቲዉ ዉስጥ የሰላም ባህል እንዲጎለብት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ነዉ፡፡በወቅቱ ስለግጭት ምንነት፣መንስኤዎች፣አመላካች ሁኔታዎችና መፍትሄዎች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎች አሰልጣኙ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በስልጠናው ማጠናቀቂያ ወቅት ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲው እየተካሄደ ያለዉ የመማር ማስተማር ሥራ አስደሳች መሆኑን በመጥቀስ ለወደፊቱም ሁሉም ተማሪ ለዩኒቨርሲቲዉ ሰላም በጋራ ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል ብለዋል፡፡

በኮምፒዉተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከ1-4ኛ አመት ድረስ በሚማሩ ተማሪዎች የተሰሩ 16 አዳዲስ የኮምፒዉተር ፕሮግራሞች በዋናዉ ግቢ እና በአባያ ግቢ ከግንቦት 11-12/2007 .ም ድረስ ለዕይታ ቀርበዋል፡፡

በዓውደ ርዕዩ ለዕይታ ከቀረቡ የኮምፒዉተር ፕሮግራሞች መካከል የዉጪ ሀገርና የሀገር ዉስጥ ጎቢኚዎች ባሉበት ሆነዉ በኢንተርኔት አማካኝነት ሆቴል ለመያዝ፣የአዉቶብስ ቲኬት ለመቁረጥ ፣ ስለቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች መረጃ ማግኘት የሚያስችላቸዉና በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተማሪዎች መመረቂያ ጽሁፎች ዝግጅት ወቅት የሚከሰቱ ኩረጃዎችን ለመቆጣጠር የሚያግዙ ፕሮግራሞች ተጠቃሾች ናቸዉ፡፡

የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ኤግዚብሽኑን በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት በኤግዚብሽኑ የቀረቡት የኮምፒዉተር ፕሮግራሞች ችግር ፈቺ ከመሆናቸዉ በተጨማሪ በተማሪዎች የግል ጥረት መሰራታቸዉ የሚበረታታ ነዉ፡፡ ዶ/ር ፈለቀ አክለዉ ተማሪዎች እንዲህ አይነት ሥራ መስራታቸዉ ከበስተጀርባቸዉ ጠንካራ መምህራን መኖራቸዉንና የዩኒቨርሲቲዉን የትምህርት አሰጣጥ ጥራት የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸዉ በኤግዚብሽኑ የቀረቡት የፈጠራ ሥራዎች ዓለም በኮምፒዉተር ዕዉቀት የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ከምናከናዉናቸዉ ተግባራት አንዱ አካል መሆኑን ጠቅሰዉ የፈጠራ ሥራዎቹ ወደ ተግባር ሊለወጡ የሚችሉ ናቸዉ ብለዋል፡፡

በአዉደ ርዕዩ ወቅት በተሳታፊዎች በተሰጠዉ ድምጽ አሸናፊ የሆነዉ በተማሪዎች መመረቂያ ጽሁፎች ዝግጅት ወቅት የሚከሰቱ ኩረጃዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ፕሮግራም በመስራት ለዕይታ ያቀረበዉ-4ኛ አመት ተመራቂ ተማሪ አቤል ተመስገን ነዉ፡፡ተማሪ አቤል እነደተናገረዉ ተመራቂ ተማሪዎች መመረቂያ ጽሁፎቻቸዉን በሚያቀርቡበት ወቅት በፊት የተመረቁ ተማሪዎች ከሰሯቸዉ ሥራዎች በተወሰነ መልኩ ኮርጀዉ ስለሚያቀርቡ በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪዎች የተሰሩ ፕሮጀክቶች አንዳንዶቹ ተመሳሳይነት ይታይባቸዋል፡፡ ስለዚህ እሱ የሰራዉ የኮምፒዉተር ፕሮግራም በኢኒስቲትዩቱ የተሰሩ ፕሮጀክቶችን በጠቅላላ መዝግቦ መያዝ ስለሚያስችል ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ሲመጡ በቀላሉ ለይቶ ያሳዉቃል፡፡ኩረጃ በአንድ የኒቨርሲቲ ብቻ የማይወሰን አለም አቀፋዊ እና ሀገር አቀፋዊ ባህሪ ስላለዉ አሁን የሰራዉን ፕሮጀክት በዚህ ደረጃ የማሳደግ ህልም እንዳለዉም ተማሪ አቤል አስምሮበታል፡፡

በአዉደ ርዕዩ መዝጊያ ስነ-ስርአት ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲዉ መምህራን፣ተማሪዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በሰጡት አስተያየት እንዲህ አይነት አዉደ ርዕይ መካሄዱ ሌሎችንም ተማሪዎች የሚያነሳሳ መሆኑን በመጥቀስ የአዉደርዕዩ አቅራቢ ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ትምህርት በተግባር አሳይተዋል ብለዋል፡፡