ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሀዋሳ ቅ/ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባር እንዲሁም በአካል ጉዳተኞች እና በሴቶች ሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ከስድስቱም ካምፓሶች ለተወጣጡ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ባለሙያዎች መጋቢት 15/2010 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በስልጠናው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለፁት በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ኢትዮጵያ የዜጎቿን ሰብዓዊ መብቶች ለማክበር ያስችላት ዘንድ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በመቀበልና የሀገሪቱ ህግ አካል እንዲሆኑ በማድረግ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው፡፡ ይህ ስልጠናም በዋናነት የሴቶችንና የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ ተዘጋጅቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የግንዛቤና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በለጠ ይልማ ኮሚሽኑ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ክትትል በማድረግ፣ ጥናትና ምርምር በማካሄድ፣ የምክር አገልግሎት በመስጠት፣ ሰብዓዊ መብቶች ተጥሰው ሲገኙ የእርምት እርምጃዎች በማስወሰድ እንዲሁም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ሚናውን እየተወጣ አንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡

በስልጠናው የኮሚሽኑ ስልጣንና ተግባር፣ የአካል ጉዳተኞችና የሴቶች ሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ የተዘጋጁ ሰነዶች ቀርበው በሰፊው ውይይት ተደርጎባችዋል፡፡