የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክን ህልውና ለመታደግ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈረመ

ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ጽ/ቤት፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የጫሞ ሐይቅ ዓሳ አስጋሪዎች ማህበር፣ በጫሞ ሐይቅ የጀልባ አገልግሎት ሰጪዎች ማህበራት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ግንቦት 24/2010 ዓ.ም የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በመሥራት የተፈጥሮ አደጋና ሰው ሰራሽ ችግሮችን በጋራ በመከላከል ብሔራዊ ፓርኩ ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ማራኪ የቱሪስት አገልግሎት የመስጠት ሥራውን ስኬታማ የሚያደርጉበትን አሠራር ለመዘርጋት ስምምነቱ መፈረሙን የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ ሽመልስ ዘነበ ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ስምምነቱ የጫሞ ሐይቅን ብዝሃ ህይወት በዘላቂነት ለመጠበቅ፣ ብዝሃ ህይወቱን የሚጎዳ ከመጠን ያለፈ አሳ ማስገርን ለመከላከል የሚያስችል ስልትን ለመቀየስ፣ ባለድርሻ አካላት የፓርኩን ውሃማ አካል ጠቀሜታ ተረድተው የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው ለማድረግ ያስችላል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ጽ/ቤት በዋናነት በጫሞ ሐይቅና አካባቢው የዱር እንስሳት ጥበቃና መጠለያ ክልሎችን ይለያል፤ ከህገ-ወጥ ድርጊቶች ይጠብቃል፤ በፓርኩ ክልልና በጫሞ ሐይቅ በተፈቀዱ ተግባራት የተሰማሩ ዓሳ አስጋሪ፣ የጀልባ እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ማህበራትን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ይከታተላል፤ ህገ-ወጥ ዓሳ ማስገርንና ሌሎች ተግባራትን ይቆጣጠራል፤ ወደ ህግ በማቅረብ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድባቸውም ያደርጋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ የዱር እንሰሳትን ወይም ውጤታቸውን በህግ በተፈቀደ መጠን ለሣይንሳዊ ተግባር ወይም ለትምህርት ያውላል፤ በፓርኩ የተፈጥሮ ሀብቶችና በሐይቁ ላይ የሚደርሱ የደለል፣ የቆሻሻና የአካባቢ መበከል መንስኤዎች ላይ ጥናቶችን በማካሄድ ወደ ተግባር ይለውጣል፡፡

በጫሞ ሐይቅና አካባቢው ጤናማና ምርታማ የሆነ የአሳ ማስገርና የተፈጥሮ ሃብት አያያዝ እንዲኖር፣ የሐይቁና የብዝሃ ህይወት ጥበቃና የአሳ አስጋሪዎች ተጠቃሚነት ዘላቂ እንዲሆን እንዲሁም የተፈጥሮ ይዘቱ ተጠብቆ ለተማሪዎችና ለተመራማሪዎች በተለይም ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃና የውሃ አዘል መሬቶች ሥነ-ህይወታዊ ሀብቶች የምርምር ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ለማድረግ ሐይቁ ላይ የሚደረገውን ያልተፈቀደ የአሳ ማስገር ማቆም እና ወደ ጫሞ ሀይቅ የሚገባውን ደለል፣ ቆሻሻ፣ ፍሳሽና ኬሚካል አሁን ካለበት በሦስት ዓመት ውስጥ 75 በመቶ መቀነስ እንዳለበት በሰነዱ ተጠቅሷል፡፡

የVLIR _IUC ፕሮጀክት ማኔጀርና የዘርፉ ተመራማሪ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለፁት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፓርኩ አካል በሆነው ጫሞ ሐይቅ የሚያጋጥሙ ችግሮች እና መፍትሔዎቻቸው ላይ ሣይንሳዊ ጥናትና ምርምር በማድረግ በጥናቱ መሠረት ፓርኩ እንዲለማና እንዲጠበቅ የበኩሉን እየተወጣ ነው፡፡ ለዚህ ሥራውም GIZ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት በቁሳቁስ ግዢና ሌሎችም መስኮች ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡

GIZ የፓርኩ ህልውና ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እና የጫሞ ሐይቅና አካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እንዲጎለብት ህግን የማስከበር፣ የአቅም ግንባታ፣ የአማካሪነት፣ ግብዓቶችንና የፋይናንስ ወጭዎችን በከፊል የመሸፈን ሥራዎችን በአጋርነት እንደሚሠራ በGIZ የብዝሃ ህይወትና የደን ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ደረጀ አበራ ተናግረዋል፡፡