18ኛው ዓለም አቀፍ የውኃ ሀብት ልማት ዓውደ ጥናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ

በአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት 18ኛው ዓለም አቀፍ የውኃ ሀብት ልማት ዓውደ ጥናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከሰኔ 1-2 ለተከታታይ 2 ቀናት ተካሂዷል፡፡  በፕሮግራሙ ከተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ኢንስቲትዩቶች እንዲሁም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጡ ምሁራን 24 ምርምሮችና 6 ፖስተሮች ቀርበዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ፣ በውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ፣ በውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የመስኖና ፍሳሽ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አብረሃም አዱኛ፣ የኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን ዳይሬክተር ጄኔራል ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ፣ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና በአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር ታረቀኝ ታደሰ እና ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የቦርድ አባላትና ምሁራን በዓውደ ጥናቱ ተገኝተዋል፡፡

የምርምር አውደ ጥናቱ ዋና ዓላማ የዘርፉን ተመራማሪዎችና ውሳኔ ሰጪዎች በጋራ በማገናኘት የሀሳብና የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ማድረግ፣ በባለድርሻ አካላቱ መካከል ተጨማሪ የግንኙነት መስመር መፍጠር እና ‹‹ውኃ ለዘላቂ ልማት›› የሚለውን መርህ ማሳካት ነው፡፡

የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል እንደተናገሩት ለሁሉም ሥነ-ህይወት የመኖር ቁልፍ ሀብት የሆነው ውኃ የግብርና፣ የኢንደስትሪ፣ የኃይል እና የትራንስፖርት ዘርፎች ውጤታማነት ወሳኝ በመሆኑ የውኃ አስተዳደር ጉዳይ ለልማት፣ ለጤናና ለማህበራዊ ዋስትና አስፈላጊ ነው፡፡

ኢንስቲትዩቱ በ32 ዓመት ቆይታው በመማር ማስተማርም ሆነ በውኃው ዘርፍ በሚያደርገው የምርምር ሥራዎች አገራዊና አለማቀፋዊ እውቅና ማግኘቱን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው በአሁኑ ሰዓት ለአገራችን ዕድገት የውኃ ዘርፍ የሚጫወተው ሚና ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ኢንስቲትዩቱ እንደ ውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ካሉ መሰል ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ዘርፉን ለማሳደግ በቁርጠኝነት ይሠራል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ሲምፖዚየሙ ለዘላቂ የውኃ ሀብት ልማት ሣይንሳዊ ምክረ ሀሳቦችን ለማንሸራሸርና የምርምር ውጤቶችና መልካም ተግባራትን ለመለዋወጥ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ፕሬዝደንቱ ገለፃ ዩኒቨርሲቲው በውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዘርፍ ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን በማፍራት፣ በጥናትና ምርምር አቅሙን በመገንባትና ዕውቀት በማመንጨት ዘላቂ የውኃ ሀብት ዕድገትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በውኃ ቴክኖሎጂ ትምህርት ዘርፍ የድህረ-ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞችን በማስፋፋት፣ የመምህራንና ሠራተኞችን የት/ት ደረጃን በማሻሻል፣ መሰረተ ልማቶችን በማሻሻል እንዲሁም ለመማር ማስተማርና ምርምር ሥራ የሚያግዙ ቤተ-ሙከራዎችን በማደራጀትና በማሻሻል ላይ የሚገኝ በመሆኑ የዘርፉ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅርበት እንዲሠሩ ጥያቄዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የልማት ሥራዎች ተጠናክረው የህዝቡ ማህበራዊ ዕድገትና ንፁህ ውኃ የመጠቀም ዕድል ሊሰፋ ይገባል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለሚገነቡ አዳዲስ ኢንደስትሪዎችና አግሮ ፕሮሰሲንግ ማዕከላት ጥጥ፣ ሸንኮራ አገዳና ሌሎች ግብዓቶችን በመስኖ ማልማት የሚገባ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በሚኒስቴር መ/ቤቱ የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ  ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ መንግሥት ለመጠጥ ውኃና ለመስኖ ልማት ሥራዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በተለያየ መንገድ እየደገፈ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የሚያደርጉትን ጥረቶች አጠናክረው በመቀጠል ከተለያየ ቋት የሚመጣውን ሀብት በማሰባሰብ በ2017 በሀገሪቱ በገጠርም ሆነ በከተማ 100% የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን የምናሳካ ይሆናል ብለዋል፡፡

ከጀርመኑ ሙኒክ ዩኒቨርሲቲ የመጡት የዓውደ ጥናቱ ተሳታፊ D/r Luk Ollan በውኃው ዘርፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ታዋቂ በሆነው ዩኒቨርሲቲ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው የውኃ ሴክተሩን ከማጎልበት አኳያ እንደዚህ አይነት መድረኮች ጠቃሚ ናቸው ብለዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የአዘጋጁ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ አዲግራት፣ አክሱም፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ሀሮማያ፣ ሀዋሳ እና ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲዎች፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም፣ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢና ልማት ጥናት ማዕከል፣ ዓለም አቀፍ የውኃ አስተዳደር ተቋም፣ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ተቋም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም የጀርመኑ ሙኒክ ዩኒቨርሲቲ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡