ለተመራቂ ተማሪዎች በአልሙናይና ትሬሰር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ኦረንቴሽን ተሰጠ

የዩኒቨርሲቲው ሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት በሁሉም ካምፓስ ለሚገኙ ለተመራቂ ተማሪዎች በአልሙናይና ትሬሰር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ኦረንቴሽን ከሰኔ 11-18/2010 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተርና የአልሙናይ አባል ዶ/ር አብደላ ከማል እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የሚያስመርቃቸው ተማሪዎች በዕውቀትና በክህሎት ብቁ በመሆናቸው በሀገሪቱ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በትላልቅ ኃላፊነቶች  ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ተማሪዎች ከተመረቁባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አልሙናይ መሆን ለዩኒቨርሲቲዎችም ሆነ ለተማሪዎች ጠቀሜታው የጎላ ስለሚሆን ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያላቸውን ቁርኝት በማጠናከር ተግተው እንዲሠሩ ዶ/ር አብደላ አሳስበዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተባባሪ ሬጅስትራር አቶ ሶፍያን አብዱልመናን እንደገለጹት የፕሮግራሙ ዓላማ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመረቁ ወዲህ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠናክሩና በትምህርት ላይ በነበሩ ጊዜም ሆነ ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመለየት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ትስስር ለመፍጠር ነው፡፡

የአልሙናይና ትሬሰር ጥናት ተባባሪ ሬጅስትራር ዶ/ር ሀብታሙ እንድሪስ እንዳብራሩት ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ ከዩኒቨርሲቲው ጋር አልሙናይ መሆን ለተማሪዎች፣ ለዩኒቨርሲቲዉና ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል፡፡ ዶ/ር ሀብታሙ ሬጅስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ተማሪዎች ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከርና ቀልጣፋ ለማድረግ የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ያመቻቸ በመሆኑ ተማሪዎች አዳዲስና የተሻሻሉ መረጃዎችንና የትምህርት ፕሮግራሞችን በቀላሉ ማግኘትና መጠቀም ይችላሉ ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ለንቁ አልሙናይ አባላት በዩኒቨርሲቲው በተከፈቱ ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ዩኒቨርሲቲው ቅድሚያ እንደሚሰጥና የክፍያ ቅናሽ እንደሚያረግም ጠቅሰዋል፡፡

በፕሮግራሙ ማጠናቀቂያ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቷል፡፡