ለሰላም ፎረም ጽ/ቤት ድጋፍ ለሰጡ አካላት የዕውቅናና የምስጋና ፕሮግራም ተዘጋጀ

የዩኒቨርሲቲው ሰላም ፎረም ጽ/ቤት በግጭት መከላከል እና በሰላም እሴት ግንባታ ላይ በግንባር ቀደምነት ላገለገሉ ተመራቂ ተማሪዎች እና ፎረሙን ሲደግፉ ለነበሩ የአስተዳደር አካላት ሰኔ 27/2010 ዓ/ም የዕውቅናና የምስጋና ፕሮግራም ተዘጋጅቷል፡፡
በፕሮግራሙ የፎረሙ ዓመታዊ ክንውን ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በሂደቱ በነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ላይ ውይይት ተደርጎ ቀጣይ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ለሰላም መስፈን አስተዋጽኦ ሊያበረክት በሚችል የፈጠራ ሥራ ላይ ገለፃ እና በሰላም ዙሪያ የተዘጋጀ ግጥምን ጨምሮ ሌሎችም ዝግጅቶች ቀርበዋል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የፎረሙ ዓላማ ተማሪዎችን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በማቀራረብ በተቋሙ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባህልን በማዳበር ተማሪዎች እርስ በእርስ፣ ከመምህራን፣ ከአስተዳደር ሰራተኞች እና ከህብረተሰቡ ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙነት በማጎልበት በሀገር ፍቅርና በሕብረ ብሄራዊነት የሚያምን እንዲሁም ለሀገር ሀብትና ንብረት ተቆርቋሪ ትውልድ እንዲፈጠር ማስቻል ነው፡፡
የዩኒቨርሲተው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሳለጥና ሰላማዊ አካባቢ እንዲኖር ፎረሙ ያከናወናቸው ተግባራት ከፍተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የፎረሙ አባል ተማሪዎችም መሠረታዊ የሆነውን ሰላምን ለማስፈን ላደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ እውቅና መስጠት ተገቢ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ ሥራው በፍላጎት በማገልገል የህሊና እርካታ ለማግኘት የሚሠራ ከመሆኑ አንጻር በሚመጣው ለውጥም የሚገኘው እርካታ ከፍ ያለ መሆኑን አውስተዋል፡፡ በፎረሙ ሲሳተፉ ለነበሩ ተማሪዎችም በየትኛውም ሁኔታ ኃላፊነትን ለመሸከም የሚያስችል አቅም የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ከሰዎች ጋር ለሚኖራቸው ሁለንተናዊ ግንኙነት ትልቅ መሠረት የሚጥል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የጋሞ ጎፋ ዞን ፀጥታና አስተዳደር መምሪያ ተወካይና የሰላም እሴት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዘኪዮስ ቦንጋ በበኩላቸው ፎረሙ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን አበረታች እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸው ችግሮች እንዳይፈጠሩ የተለያዩ ተግባራትን ከማከናወን ባለፈ ተፈጥሮ ሲገኝም እንዳይባባስ በማድረግና ሰላማዊ አካባቢ እንዲኖር በማስቻል ረገድም ትልቅ ሥራ መሰራቱን ገልፀዋል፡፡ ፎረሙ ከመምሪያው ጋር በቅንጅት መሥራቱ ለዩኒቨርሲቲው ብቻም ሳይሆን ለአካባቢው ሰላም ከፍተኛ አስተዋጥኦ ያበረከተ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በትምህርት ዘመኑ የነባርና አዲስ ተማሪዎች ቅበላ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈፀም የጎላ ድርሻ ከመወጣት ጀምሮ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ሲሠራ መቆየቱን የፎረሙ ፀሐፊ ተማሪ ነስረድን ሐምዛ ገልጿል፡፡ ፎረሙ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የመጥፎ ኩነቶች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ግንዛቤ የመፍጠር፣ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በግልጽ በመወያየትና በመከባበር የመፍታት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የሰላም ባህል እንዲሰፍንና ተጠናክሮ  እንዲቀጥል ሲሰራ መቆየቱንም ተናግሯል፡፡
በትምህርት ዓመቱ ከታዩ ችግሮች መካከል የግለሰብ አለመግባባት ወደ ቡድን መቀየር፣ የአባላት የሥራ ላይ ክህሎት ማነስ፣ ተማሪዎች መጠጥ በመጠጣት የመረበሽ፣ የምግብ አቅርቦት አገልግሎት ላይ የሚፈጠሩ አንዳንድ ክፍተቶች እና የስርቆት መበራከት በዋናነት ተጠቅሰዋል፡፡
በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው አመራር አካላት፣ የፎረሙ አባላትና ሌሎችም የተሳተፉ ሲሆን በዓመቱ ለፎረሙ ሥራ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ሰላም ፎረም ሳውላ ካምፓስን ጨምሮ በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ካምፓሶች አደረጃጀቶች በመፍጠር ሰላማዊ የመማር ማስተማር አካባቢ እንዲፈጠር እየሠራ ይገኛል፡፡