በከፍተኛ ዲፕሎማ መርሃ ግብር/HDP/ የሰለጠኑ መምህራን ተመረቁ

የዩኒቨርሲቲው የስነ - ትምህርትና ስነ - ባህርይ ሣይንስ ትምህርት ቤት በ2010 ዓ/ም በከፍተኛ ዲፕሎማ መርሃ ግብር/HDP/ ለ1 ዓመት ያሰለጠናቸውን 147 የዩኒቨርሲቲው መ/ራን ሐምሌ 5/2010 ዓ/ም በዲፕሎማ አስመርቋል፡፡

 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው የማስተማር ጥበብ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ ለተማሪዎች መውደቅ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው መ/ሩ ስለሆነ በሁሉም የትምህርት መስኮች ያሉ መ/ራን የከፍተኛ ዲፕሎማ መርሃ ግብር ፕሮግራምን ትርጉም ባለው ደረጃ ተከታትለው በማጠናቀቅና ክፍተቶችን በመሙላት በተማሪዎች ውጤት ላይ ከፍተኛ መሻሻል ሊታይ  እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ይህም የዩኒቨርሲቲውን የትምህርት ጥራት ከማስጠበቅ አንፃር ትልቅ ዋጋ እንዳለው ገልፀው ስልጠናውን ሳያቋርጡ የጨረሱ መ/ራንን፣ አሰልጣኞችንና አስተባባሪውን እንዲሁም ት/ቤቱን አመስግነዋል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

HDP የመ/ራንን የሙያ ክሂል በማሻሻል የትምህርት ጥራትን እንደሚያሳድግ የገለፁት የስነ - ትምህርትና ስነ - ባህርይ ሣይንስ ትምህርት ቤት ዲን ዶ/ር ኢዮብ አየነው  መ/ራን በራሳቸው ፍላጎት ሙያቸውን፣ ስነ-ምግባራቸውንና በንድፈ ሀሳብ ላይ የተመሰረተ ተግባራዊ የማስተማር ክህሎትን እንዲያዳብሩ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ለተቋሙና ለማህበረሰቡ ዕድገት መልካም አርዓያ እንዲሆኑ፣ ደረጃውን የጠበቀና ከፍተኛ ጥራት ያለው የማስተማር ልምድ እንዲያዳብሩ፣ ለተግባራዊ ምርምርና ለቡድን ስራ እንዲሁም ለፆታ እኩልነትና አካቶ ትምህርት ራሳቸውን ዝግጁ እንዲያደርጉ የሚረዳ ነው፡፡

የፕሮግራሙ አስተባባሪ መ/ር አንለይ ብርሃኑ የከፍተኛ ዲፕሎማ መርሃ ግብር ሙያውን ለማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው መ/ራን ለስልጠናው ጥሩ አመለካከት ሊኖራቸው፣ በንቃት ሊሳተፉ እንዲሁም በአግባቡ ተከታትለው ሊጨርሱ እንደሚገባና ስልጠናውንም መውሰድ ግዴታ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ተመራቂ መ/ራን ከመማር ማስተማርና ከምርምር ስራችሁ በተጨማሪ ባላችሁ ጊዜ ስልጠናው ትልቅ ተግባር መሆኑን ተገንዝባችሁ በስኬት በማጠናቀቃችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡ ስልጠናው በክፍል ውስጥ ለተማሪዎች ተግባራዊ ሲደረግ ጥሩ የመማር ማስተማር ሁኔታ እንዲፈጠርና ተማሪዎች ያለምንም መሰላቸት ውጤታማ እንዲሆኑ የሚረዳ መሆኑን ገልጸው ተማሪዎቻችን ውጤታማና የሀገርን ችግር የሚፈቱ እንዲሆኑ መጀመሪያ የሚያስተምረው መ/ር በትክክል የማስተማሪያ ስነ-ዘዴን ተጠቅሞ ማስተማርና እውቀት ማስጨበጥ አለበት ብለዋል፡፡

ተመራቂ መ/ራን በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ረጅም ጊዜ በመውሰዱ አሰልቺነት ቢስተዋልበትም ለክፍል ውስጥ ትግበራ ወሳኝ የሆነ በቂ የማስተማር ክህሎትና ዕውቀትን እንዲጨብጡ ያስቻላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም በስልጠናው ወቅት ከተከናወኑ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች መካከል በHDP ላይ የተከናወነ የተሻለ ችግር ፈቺ ጥናታዊ ፅሁፍ ተመርጦ የቀረበና አስተያየት የተሰጠበት ሲሆን ለተመራቂዎችና ለአሰልጣኞችም የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡