አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ FES ከተባለ የጀርመን ድርጅት ጋር በመተባበር ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄደ

ዩኒቨርሲቲው Friedrich–Ebert–Stiftung (FES) ከተሰኘ የጀርመን ድርጅት ጋር በመተባበር አሁን ላይ ባለው የሀገራችን ፖለቲካ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ሀገራዊ ውይይት ህዳር 8/2011 ዓ/ም በኤሜራልድ ሆቴል አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በማህበራዊና ሥነ-ሰብ ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር ዩኒቲ አስተባባሪ መ/ር ሣልሳዊ ፈለቀ እንደገለፁት የሀገራችንን ምሁራንና አመራሮችን ያሳተፉ ፖለቲካዊ ውይይቶች የተጀመረውን አገራዊ አንድነትና ለውጥ ከማጠናከር አንፃር ሚናቸው የጎላ በመሆኑ ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ መሰል የውይይት መድረኮችን ያዘጋጃል ብለዋል፡፡

የአስተዳደርና ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር መልካሙ ማዳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህዝቦች የጀግንነት ተምሳሌት የሆነች የታሪክ ማህደር መሆኗን አስታውሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች አንድነታችንን የማይገልፁና ከኢትዮጵያዊነት ባህል ያፈነገጡ ናቸው፡፡ ም/ፕሬዝደንቱ አክለው የውይይቱ ተካፋይ እንግዶች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና  ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በቂ ውይይት በማድረግ አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን ለማየት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በበኩላቸው የሀገር ፍቅር ስሜት ያለው፣ ባህሉንና ቋንቋውን ብቻ ሳይሆን ታሪኩን የሚረዳ ትውልድ ለመፍጠር በአድዋ ድል ወቅት የነበረውን መተሳሰብና አንድነት አሁን ላይ በማምጣት የተሻለች ኢትዮጵያን ልንገነባ ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹በጋራ ያልቆመ ህዝብ ይወድቃል›› ያሉት የህግ ት/ቤት ዲን አቶ ደርሶልኝ የኔአባት ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች በእኩልነት ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማት ማረጋገጥ፣ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ህጎችን ማሻሻል እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችንን ህገ-መንግስቱን የጠበቀ እንዲሆን ማስቻል ብሄራዊ መግባባትና አንድነት እንዲጠናከር ጉልህ ድርሻ ይጫወታል ብለዋል፡፡

ብሄራዊ አንድነት የሰው ልጅ በአንድ ሀገራዊ አስተሳሰብ፣ ብሄራዊ ማንነቱንና ክብሩን አስከብሮ፣ እርስ በእርስ ተከባብሮ መኖር እንደሆነ የገልፀው አርቲስት ሚካኤል ሚሊዮን በዚህ ረገድ የሀገራችን አርቲስቶች ሀገራዊ  አንድነትን የሚያጠናክሩ ጥበባዊ ሥራዎችን በመሥራት ሀገራዊ አንድነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ በበኩላቸው ከመቻቻል በላይ ማገናዘብ እንደሚበልጥ ጠቅሰው  አንዳችን የሌላውን ባህል፣ ቋንቋና እምነት በማወቅ የአንዱ ጉዳት እንደ ራሳችን ጉዳት እስከሚያሳስበን ድረስ ለሀገራዊ አንድነታችን መጠናከር መስራት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡት የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው አብዛኞቹ  በሀገራችን የተፃፉ  ታሪኮች የሰሜን ኢትዮጵያን ታሪክ ብቻ አጉልተው ማውሳታቸውና የሀገራችን መሪዎች ሥልጣን ላይ ሲመጡ ከኔ ወዲያ ሌላ በሚል አመራር የዲሞክራሲው ዕድገት እንዳይፈጥን በማድረግ ብሄርተኝነት እንዲሰፍንና ሀገራዊ አንድነት እንዳይጠናከር አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥረዋል ሲሉ ሃሳበቸውን ሰጥተዋል፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ኃላፊዎችና መምህራንን ጨምሮ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት፣ ከFriedrich-Ebert-Stiftung ድርጅት፣ ከኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት ኤጀንሲ፣ ከአዲስ አበባ  ዩኒቨርሲቲ  የፍልስፍና፣ የፖለቲካ ሳይንስና የህግ ምሁራን እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ከተማና ከጋሞ ጎፋ ዞን የተወጣጡ ተሳታፈዎች ተገኝተዋል፡፡