የዩኒቨርሲቲው IUC ፕሮጀክት በጫሞ ሐይቅ ላይ የዓሳ ሀብት መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ ከነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የጀመረው ሥራ ውጤት እያሳየ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የIUC ፕሮጀክት ኃላፊና የዘርፉ ተመራማሪ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለፁት በዋናነት የሐይቁን ዓሳ ሀብት ወደ ነበረበት ለመመለስ 100 ሄክታር የሚሆነውን የሀይቁን ክፍል በመከለል ቦታው ከሰው ንክኪ ነፃ እንዲሆን በማድረግ እንዲሁም በሐይቁ ዙሪያ ያሉ ሀገር በቀል እፅዋትን በመትከል ጥበቃ በመደረጉ በከፍተኛ ሁኔታ የዓሳው ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህም ውጤት የዓሳ ሀብቱን ከመጨመር ባሻገር በጋራ መሥራት ከቻልን ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አመላካች ነው ብለዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለፃ የሀይቁ ዙሪያና ተፋሰስ የሚገኙ ደኖች መራቆታቸው፣ ተገቢው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ አለመሠራቱ፣ በሐይቁ ዙሪያ የሚገኙ ተዳፋት መሬቶች መታረሳቸው እንዲሁም ከሐይቁ አቅም በላይ የሆኑ አስጋሪዎች በሐይቁ ላይ መኖራቸው መሰረታዊ ችግሮች ናቸው፡፡

በሐይቁ ላይ ያለው የዓሳ ማስገር ሂደት ሥርዓት ሊበጅለት ይገባል ያሉት ዶ/ር ፋሲል በዚህ ረገድ በሐይቁ ላይ ያለውን የዓሳ ሀብት መጠን በመለየት ምን ያህል የሰው ኃይል በሐይቁ ላይ በአስጋሪነት መሰማራት እንዳለበት የሚያመላክት ምርምር እየተሠራ በመሆኑ ሥራው ሲጠናቀቅ የአስጋሪዎች ቁጥርን የማመጣጠን ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየሠራ ሲሆን ወደ ሐይቁ የሚገባውን ደለል ለመከላከል ያግዝ ዘንድ የሀይቁ ተፋሰስ የሆኑት የኤልጎና ሲሌ ተፋሰሶችን በማልማት ከመነሻው ችግሩን ለማስቆም እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሐይቁ ላይ የሚታዩት ችግሮች በዩኒቨርሲቲው አቅም ብቻ የሚቀረፉ እንዳልሆኑ የገለፁት ዶ/ር ፋሲል ችግሩ የሁሉንም ህብረተሰብ ርብርብ እንዲሁም የፖሊቲካ አመራሩን ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል፡፡