በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሲቪል ምህንድስና ፋከልቲ ከኢትዮጵያ ሲቪል ምህንድስና ተማሪዎች ማኅበር አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ጋር መተባበር በዘንድሮው ዓመት ፋከልቲውን ለተቀላቀሉ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ እና ስለፋከልቲው የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ታኅሣሥ 1/2011 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡

በፋከልቲው የሲቪልና የሰርቬይንግ ትምህርት ክፍሎች አዲስ ለተቀላቀሉ ተማሪዎች ትምህርት ክፍሎቹን፣ ውጤት አያያዝ፣ ሲቪል ምህንድስና ማኅበር እንዲሁም አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን በተመለከተ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን የፋከልቲው ዲን አቶ ሐብታሙ መለሰ ገልፀዋል፡፡ ይህም በተማሪዎች፣ በመምህራን እንዲሁም በፋከልቲው መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር በማድረግ የመማር ማስተማሩ ሥራ እንዲሳለጥ ብሎም ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው በሚኖራቸው ቆይታ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲጎለብት በማገዝ፣ ለአገራዊ ለውጡ እንቅፋት ሊሆኑ ከሚችሉ ተግባራት ራሳቸውን በማራቅና ሌሎች አርአያ የሚሆኑ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ብሎም ለትምህርታቸው ትኩረት በመስጠት ውጤታማ መሆን እንደሚገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ስለ ትምህርት ክፍሎች፣ የውጤት አያያዝ ሂደት እና የዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ጉዳዮችን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ምህንድስና ተማሪዎች ማኅበር ዓላማ፣ ተልዕኮ እና ዝርዝር ተግባራት በዩኒቨርሲቲው የማኅበሩ አባል ተማሪዎች ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል በመማር ማስተማርና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ከፋከልቲው ዲን እና ከክፍል ተጠሪ መምህራን ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡

በተማሪዎች የተነሱ በተለይም የኮርስ አሰጣጥ፣ በክፍል ጥበት ምክንያት የሚፈጠረው ሙቀት በመማር ማስተማር ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እና ሌሎች ችግሮችን አስመልክቶ በፋከልቲው ዲንና በመምህራኑ ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ከዚህ ባሻገር ያሉ በበላይ አመራሮች ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮች በማቅረብ በሚፈቱበት አግባብ ላይ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚሠራ ቃል ገብተዋል፡፡

ተሳታፊ ተማሪዎች በፋከልቲው በታየው የአጋርነት መንፈስ ደስ መሰኘታቸውን ገልፀው በዩኒቨርሲቲው ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መጠናከር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ቃል ገብተዋል፡፡

በፕሮግራሙ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አመራሮች፣ የፋከልቲው ዲን፣ መምህራን እንዲሁም የፋከልቲው አዲስ እና  ነባር ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡