የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካሄደ

የ2011 ዓ/ም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማኅበር መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከታህሳስ 25-26/2011 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡
የአርባ  ምንጭ  ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ የስፖርት ፌስቲቫሎች ሰፊ በሆነው የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ መካከል ብሎም በሀገር ደረጃ ለህዝቦች አንድነትና መዋደድ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

በ2010 ዓ/ም በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በተካሄደው የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ስምንት አጀንዳዎች  በቃለ-ጉባኤው የተካተቱ ሲሆን በአዲስ መልክ የተዘጋጀውን የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ፣ የኦዲት ሪፖርት ማድመጥ፣ የአገር አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ዝግጅትና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ተወያይቶ የዘንድሮው ጉባዔ የትኩረት ነጥቦች መሆናቸውን የማኅበሩ ፕሬዝደንት አቶ አባይ በላይሁን ገልፀዋል፡፡   
ማህበሩ በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ምቹ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲገነቡ ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር የአባል ተቋማት የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች አቅም እንዲገነባና ከአመለካከት አኳያም የተሻለ ግንዛቤ እንዲፈጠር ማድረግ መቻሉን አቶ አባይ አውስተዋል፡፡ ባለፉት 3 ዓመታት በአገራችን ባለው አለመረጋጋት የስፖርት ፌስቲቫሎች ሳይካሄዱ መቆየታቸውንና ለቀጣይ በተሻለ አሠራር ለማከናወን እየተሰራ መሆኑንም ፕሬዝደንቱ ገልፀዋል፡፡
በ2010 ዓ/ም 9ኛው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል በስኬት መጠናቀቁ እንዲሁም በውድድሩ ተሳታፊ ከነበሩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በእግር ኳስ አሸናፊ የሆነው የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በዓለም የዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ሻምፒዮና አገራችንን ወክሎ በተያዘው ዓመት በቻይና መሳተፍ መቻሉ ከተግባራቱ መካከል የሚጠቀሱ መሆኑን አቶ አባይ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በቴክኒክና ልማት የሥራ ሂደት የሴቶች እግር ኳስ ልማት ኃላፊ ወ/ሪት አልማዝ ፍሰሃ በበኩላቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኢንስትራክተሮችን በመላክ ለመምህራንና ለተማሪዎች የዳኝነት ሥልጠና በመስጠት፣ ዳኞችን በመላክና በማህበሩ የሚያካሄዱ ውድድሮች የሥነ-ሥርዓት ደንብ ሂደት ላይ እገዛ ማድረግ የማህበሩን እንቅስቃሴ መደገፉን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ከዩኒቨርሲቲዎች ባሻገር ባሉ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎችም የማኅበረሰብ ክፍሎች  በስፖርቱ ዘርፍ የሚጠበቀውን ለውጥ ለማጠናከር ከማኅበሩ አባል ተቋማት ተወካዮችና ባለሙያዎች ጋር በጋራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
መንግስት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋት በሰጠው ልዩ ትኩረት የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱ ከ15 በላይ በሆኑ የስፖርት ዓይነቶች ከ38 በላይ ዩኒቨርሲቲዎችን በአንድ ቦታ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ማሳተፍ ከጊዜ፣ ከፋይናንስና ከሰው ኃይል አንፃር በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት ተዳሷል፡፡
ችግሮቹን ለመፍታት አዲስ የውድድር መዋቅር በመዘርጋት በዩኒቨርሲቲዎች መካከል የሚደረገው የተማሪዎች የስፖርት ጨዋታ የታለመለትን ዋና ዓላማ እንዲያሳካና ሀገሪቱ ያለባትን የስፖርት ዕድገት ከፍተት እንዲያሟላ ማስቻል በማስፈለጉ አዲስ የውድድር መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡በመመሪያው መሠረት በተዘጋጀው የክላስተር አደረጃጀት ዩኒቨርሲቲዎች ባሉበት የዞን ክላስተር ውድድር አድርገው በቀጣዩ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው የዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ጨዋታ ላይ ይሳተፋሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማኅበር በ1999 ዓ/ም በአዲስ መልክ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 10 ዓመታት ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን 38 አባል ዩኒቨርሲቲዎች በሥሩ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ መልክ ሥራ ከጀመሩ ዩኒቨርሲቲዎች መካከልም ቦንጋ፣ ጂንካ እና ወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች የአባልነት ጥያቄ አቅርበው በጉባኤው ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡
የጉባኤው ተሳታፊዎች ከማኅበሩ ስያሜና ባለቤትነት፣ ከሥራ ክፍፍልና ወሰን፣ ከስፖርት ውድድር ባሻገር በሌሎችም ተግባራት ላይ ካለው አስተዋጽኦ፣ ስፖርቱ አገራዊ ይዘት እንዲይዝ ከማድረግ እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ከማጠናከር አኳያ ባሉ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን አንስተው ውይይት አድርገዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በቆየው ጉባኤ ላይ የማኅበሩ አባል ከሆኑ ከ38 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ አካላት፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራር አካላት እንዲሁም  የትምህርት ባለሙያዎችና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት