አዲሱ የሠራተኞች የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት የደመወዝ ስኬል አፈጻጸም መመሪያ ጥቅምት ላይ ተግባራዊ ይደረጋል

አዲሱን የሠራተኞች የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት የደመወዝ ስኬል አፈጻጸም መመሪያን በጥቅምት ወር ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ገለፀ፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ እንደገለፁት አጠቃላይ የድልድል ሥራው ከመሠራቱ አስቀድሞ በአፈፃፀም መመሪያው ዙሪያ በስፋት ለሠራተኞች ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በዳይሬክቶሬቱ ባለሙያዎች እንዲሁም ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ከፍተኛ ባለሙያዎችን በመጋበዝ የተፈጠሩ ብዥታዎችን የማጥራት ሥራ መሠራቱን አስታውሰዋል፡፡ በአፈጻጸም መመሪያው መሠረትም የደልዳይና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች ተዋቅረው እንደነበርም ገልፀዋል፡፡

ለዩኒቨርሲቲው 6,132 የሥራ መደቦች ተፈቅደው እንደነበር ያስታውሱት ዳይሬክተሯ ከእነዚህም መካከል በአፈፃፀም መመሪያው መሠረት አዲስ የተቀጠሩ፣ በትምህርት ላይ ያሉ እንዲሁም በዲሲፕሊን ቅጣት ምክንያት በውድድሩ የማይሳተፉ ሠራተኞች የሥራ መደቦችን በማስቀረት 5,743 የሥራ መደቦች በሁሉም ካምፓሶች ለውድድር ይፋ ሆነው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ከሥራው ውስብስብነትና ለውድድሩ የሚያስፈልጉ የሠራተኛው መረጃዎች ተጠናቅረው ባለመገኘታቸው ሳቢያ የድልድል ሥራው ረጅም ጊዜ ወስዶ እንደነበር የተናገሩት ወ/ሮ ከአምላክነሽ 3,656 ሠራተኞች እንደተመደቡ እንዲሁም ምደባውን ካገኙ ሠራተኞች መካከል 65 በመቶው በፍላጎታቸው ማለትም በ1ኛና 2ኛ ምርጫቸው ቀሪዎቹ 35 በመቶ ሠራተኞች ደግም የትምህርት ዝግጅታቸውንና የሥራ ልምዳቸውን መሠረት በማድረግ በኮሚቴው ተመድበዋል ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በኮሚቴው ከተመደቡ 1,369 ሠራተኞች መካካል 853 ያህሉ ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን የቀረቡትን ጥያቄዎች በተዋቀረው የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ከተመረመሩ በኋላ ኮሚቴው መጋቢት ወር ላይ ውጤቱን ይፋ አድርጓል፡፡ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ 14 ሠራተኞች ለሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርበው 9ኙ ለዩኒቨርሲቲው፣ 3ቱ ለሠራተኞቹ የተወሰነ ሲሆን የአንድ ሰው ጉዳይ በሂደት ላይ ነው፡፡

በአዲሱ ምደባ ከፍ ባለ መደብ የተመደቡ ሠራተኞችን በተመለከተ ያለውን የደመወዝ ልዩነት እንዲያገኙ የሚል የአፈፃፀም መመሪያ መተላለፉን የተናገሩት ዳይሬክተሯ ሠራተኞቹ የደመወዝ ልዩነቱን ማግኘት የሚችሉት በቀድሞው ደረጃ ለመደቡ የሚያስፈልገውን ተፈላጊ ችሎታ ማሟላታቸው እየተረጋገጠ ነው ስለሚል የማጣራቱ ሂደት ሰፊ ጊዜ ወስዷል ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ሥራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለበላይ አካል ለውሳኔ መቅረቡንና ከመስከረም 1/2011 ዓ/ም - ሰኔ 30/2011 ዓ/ም መስፈርቱን ላሟሉ ሠራተኞች የልዩነት ክፍያው በቅርቡ የሚፈፀም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አዲሱ የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናት የደመወዝ ስኬል መመሪያ ፀድቆ ለዩኒቨርሲቲው እንደተላከ የተናገሩት ዳይሬክተሯ የመምህራንን ጨምሮ መመሪያውን ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ መመሪያው በአዲሱ የምዘና ዘዴ ደረጃ ለወጣላቸው የሥራ መደቦች ደመወዝ የሚሰጥ እንጂ የደመወዝ ጭማሪ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክቶሬቱ በ2012 በጀት ዓመት ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት ይቻለው ዘንድ ዳይሬክቶሬቱን በአዲስ መልክ ለተቀላቀሉና ለነባር ሠራተኞች ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ በበጀት ዓመቱ በደንብ ልብስ አቅርቦት ላይ የሚታይ መዘግየትን ለመቅረፍ እንዲሁም በዲጂታል የሠራተኞች የሰዓት ቁጥጥር ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከICT ዳይሬክቶሬት እና ከኮምፒውተር ሣይንስ ትምህርት ክፍል ጋር በጋራ ይሠራል ብለዋል፡፡ አዲሱ የደመወዝ መመሪያ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ በቅጥርም ሆነ በደረጃ ዕድገት በጎደሉ መደቦች ላይ ሠራተኞችን የማሟላት ሥራ እንደሚሠራም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት