በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ መልካም አፈፃፀም መመዝገቡን የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ገልጿል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እንዳሉት በግማሽ ዓመቱ በዋናነት በሂደት ላይ ካሉ 421 የምርምር ፕሮጀክቶች ውስጥ 92ቱ በዚህ ዓመት የፀደቁ ናቸው፡፡ የሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት በጋሞና በጎፋ ዞኖች ውስጥ በርካታ ጤና ጣቢያዎችና ት/ቤቶች የፀሐይ ታዳሽ ኃይል ተደራሽ እያደረገ ነው፡፡ ረንረስ (RUNRES) ፕሮጀክት በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ያሉ ሙዝ አምራች አርሶ አደሮችን ከከተማው ነዋሪዎች ጋር በማስተሳሰር ገጠሩ ከተማውን ሲመግብ ከተማው ተረፈ ምርቶችን ወደ ገጠሩ በመመለስ እንዲሁም የመፀዳጃ ቤት ቆሻሻዎችን በሣይንሳዊ መንገድ ማዳበሪያ አድርጎ ለምርታማነት በመጠቀም አርሶ አደሮቹ የተሻለ ምርት አምርተው ለአገር ውስጥና ለውጭ አገራት ገበያዎች እንዲያቀርቡ እየሠራ ይገኛል፡፡ ቤኔፊት ሪያላይዝ (BENEFI-REALISE) በተለይ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በምዕራብ አባያ ወረዳ በያይቄና በዛላ ጉትሻ ቀበሌ፣ በደራሼ ወረዳ በሆልተ ቀበሌ፣ በቁጫ ወረዳ ጋሌ ቀበሌ እና በጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ ሜላ ባይሳ ቀበሌ የአየር ሁኔታውንና በሽታ ተቋቁመው በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ የሚሆኑ የአደንጓሬ፣ በቆሎ፣ ድንችና ማሽላ ምርጥ ዘሮችን በማወዳደርና በመለየት ለአርሶ አደሮች በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

በቴክኖሎጂ ሽግግር በኩልም ዘመናዊ የወተት መናጫ፣ የበቆሎና ለውዝ መፈልፈያ እንዲሁም የእንሰት መፋቂያ ቴክኖሎጂዎች ሙከራ የተደረገባቸው ሲሆን በሂደት ወደ ማኅበረሰቡ የሚወርዱ ይሆናል፡፡

የውሃ ምርምርና ልማት አንዱ የዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል ሲሆን ከአደረጃጀት አንፃር የውሃ ሀብት ምርምር ማዕከል ተቋቁሞ እየተሠራ ይገኛል ያሉት ዶ/ር ስምዖን ይህንንም በሰው ኃይልና በግብዓት የበለጠ በማደራጀት በማዕከሉ የሚሠሩ ተመራማሪዎችን አቅም በትምህርትና ስልጠና ማጎልበት፣ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራን በስፋት የሚሳተፉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዲሁም ከአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የመሥራት ልምድ ማካበት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በምርምርና ማኅበረሰብ ዘርፍ ሴቶችን የማሳተፍ መጠን እየጨመረ የመጣ ሲሆን እስከ 2ኛው ሩብ ዓመት ድረስ የሴቶች የምርምር ተሣትፎ ከ46.2 % በላይ ሆኗል፡፡ ከእነርሱም መካከል 12ቱ የምርምሩ መሪ ናቸው፡፡ በኃላፊነት ደረጃ በዘርፉ ካሉ ቦታዎች 6ቱ በሴቶች የተያዙ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ላይ ያሉ ሴት መምህራንን በክረምት ኮርስ የበለጠ ብቁ የማድረግ ስልጠና ይሰጣል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በግማሽ ዓመቱ የዩኒቨርሲቲውን ጆርናሎች ጨምሮ በተለያዩ ጆርናሎች 41 ምርምሮችን ያሳተመ ሲሆን በዚህም በዓመቱ ውስጥ ለማሳተም ከታቀደው ከግማሽ በላይ ያህሉን አሳክቷል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለአገራችን እድገት ጠቃሚ የሆኑ ምርምሮች ይሠሩበታል ተብሎ በመታመኑ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብሎ መመረጡን የተናገሩት ዶ/ር ስምዖን በመሆኑም ራስን ከማብቃት ጀምሮ በተለይም የልህቀት ማዕከላት ተብለው በተለዩ ላይ ትኩረት ሰጥተን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ቋሚ ተመራማሪዎችን በሚፈለገው መጠን በገበያ ላይ አለማግኘት፣ የመምህራን በማስተማር ሥራ ላይ መጠመድ፣ ከግብዓት አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ የቤተ - ሙከራ አደረጃጀትና የምርምር ላቦራቶሪ ግንባታና ማስፋፊያ ችግሮች በግማሽ ዓመቱ አፈፃፀም የታዩ ደካማ ጎኖች መሆናቸውን ዶ/ር ስምዖን ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት