ዩኒቨርሲቲው ከፀጋ-ብሎት የኪነ-ጥበብ ማኅበር ጋር በመተባበር የ124ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ‹‹አድዋን እየዘከርን በፍቅር ጥላቻን እንግደል›› በሚል መሪ ቃል ከየካቲት 21-23/2012 ዓ/ም በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል፡፡ ማስ ስፖርት፣ የጽዳት ዘመቻ፣ የአደባባይ ትዕይንት፣ የዝክረ-አድዋ የኪነ-ጥበብና ሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች እንዲሁም የፓናል ውይይት የክብረ በዓሉ አካል ነበሩ፡፡

የመታሰቢያ በዓል ልዩ ፕሮግራሙን የከፈቱት የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች አድዋ ኢትዮጵያ በጣሊያን ላይ የተቀዳጀችው ድል ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሉዓላዊነት የፅናትና የቆራጥነት ተምሳሌት እንደሆኑ ያስመሰከሩበት ታላቅ ገድል ነው ብለዋል፡፡ ምስሉን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ቀደምት አባቶችና እናቶች በአድዋ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው በክብር ያስረከቡንን አገር ወጣቱ ትውልድ በአንድነት መንፈስ ሊጠብቃት ይገባል ብለዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ በዓሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲከበር ጉልህ አስተዋጽዖ ላበረከቱ የፀጋ-ብሎት የኪነ-ጥበብ ማኅበር አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የፀጋ-ብሎት የኪነ-ጥበብ ማኅበር ተጠሪ ወጣት ስሜነህ ኃ/ሚካኤል የአድዋ ድል ለመላው ጥቁር ህዝቦች ታላቅ ኩራትና ድል መሆኑን ገልጾ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሉዓላዊነት የዓላማ ፅናት ያሳዩበት ትልቅ ገድል እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ወጣት ስሜነህ ዩኒቨርሲቲው ማኅበሩን ከዚህ በፊት እንደሚደግፍ ሁሉ በቀጣይም ወጣቱን ትውልድ በመልካም ስብዕና ለመገንባትና የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡

ከታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል የተወጣጡ መምህራን የአድዋን ድል በማስመልከት የአድዋ ጦርነት መንስኤ፣ ድል፣ የጣሊያኖች መሸነፍ ምስጢር፣ የጦር ኪሳራዎች እንዲሁም ታሪካዊ ፋይዳ ላይ የሚያተኩሩ የፓናል ውይይት መነሻ ጽሑፎች አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደገርጎባቸዋል፡፡ መ/ር ካሱ ጡሚሶ የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሉዓላዊነት ቀናኢ ሆነው በአንድነት መንፈስ መቆማቸውን እንደሚያመላክት ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይም መ/ር መሐመድ ሰይድ የአድዋ ድል የመላው ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ቀንዲል እንደሆነ ጠቅሰው ወጣቱ ትውልድ ተባብሮና ጠንክሮ በአንድነት ለአገሩ መቆምና በልማቱ ዘርፍ የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት ብለዋል፡፡

የፕሮግራሙ ታዳሚዎች በበኩላቸው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በዚህ መልኩ በድምቀት መከበሩ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ትምህርት እንደሆነ ገልጸው ወጣቱ ከዚህ በዓል ወኔ በመሰነቅ የአገሩን ሉዓላዊነት ማስቀጠል እንደሚገባው ገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የጋሞ የአገር ሽማሌዎች፣ ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ጋሞ ጎፋ ቅርንጫፍ የተወጣጡ እናትና አባት አርበኞች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በዓሉን ታድመዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት