በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራንና ሐኪሞች አማካኝነት በጎፋ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች ለተወጣጡ 60 የህክምና ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል፣ ቁጥጥርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከግንቦት 4-5/2012 ዓ/ም ድረስ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የቆየ ሥልጠና በሳውላ ከተማ ተሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት ይህንን ይጫኑ

ሥልጠናው የኮሮናቫይረስ ምንነት፣ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች፣ የህክምና አሰጣጥ፣ በህክምና አሰጣጥ ዙሪያ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎችና ከህክምና ባለሙያዎች በሚጠበቅ ሙያዊ ሥነ-ምግባር ዙሪያ ያተኮረ ነው፡፡

ሥልጠናውን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት በዩኒቨርሲቲው የሳውላ ካምፓስ ኃላፊ አቶ ገ/መድኅን ጫሜኖ እንዳሉት የኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የህክምና ባለሙያዎች ሚና ወሳኝ ስለሆነ ባለሙያዎቹ ከሥልጠና የሚያገኙትን ዕውቀት በመጠቀምና ራሳቸውን በሥነ-ልቦና ዝግጁ በማድረግ መንግስትና ሕዝብ የጣለባቸውን ትልቅ ኃላፊነትና አደራ ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺይፍ አክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ሥልጠናው ለኮሮናቫይረስ መከላከልና ህክምና ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰው በሌሎች አካባቢዎችም መሰል ሥልጠናዎችን ለጤና ባለሙያዎች የመስጠት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከሥልጠናው በወረርሽኙ ዙሪያ ጥሩ ግንዛቤ እንዳገኙ ገልፀው ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው በማጋራት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት