የቤኒፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም ክልላዊ የአማካሪ ምክር ቤት ጉባዔ በመስክ ጉብኝትና የ2020 የ6 ወራት ሪፖርት ግምገማ በማድረግ ከነሐሴ 26 - 27/2012 ዓ/ም ለሁለት ቀናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የሐዋሳና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮጀክት አፈፃፀም ቀርቦ ተገምግሟል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም ኃላፊ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ 2020 በጀት ዓመት የፕሮጀክቱን ዓላማዎች መሠረት ያደረጉ በርከት ያሉ ሥራዎች ታቅደው ሲሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰው በዚህም በአርሶ አደሩ ዘንድ ለውጦች እየታዩ ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የተለያዩ ሳይንሳዊና በምርምር የተረጋገጡ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አርሶ አደሩ በማቅረብ በዋናነት የሴፍትኔት ተረጂ አርሶ አደሮችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚሠራው ፕሮጀክቱ ከዚህ አንፃር የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ ምርጥ ዘር፣ ማዳባሪያና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አርሶ አደሩ እንዲጠቀም በማድረግ በአርሶ አደሩ ሕይወት ላይ ለውጥ እንዲመጣ ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በቀሪዎቹ 4 ወራት ለ1,600 አርሶ አደሮች የጓሮ አትክልት፣ ለ800 አርሶ አደሮች ዴሾ የተሰኝ ለአፈር ጥበቃና ለከብቶች መኖ የሚሆን የሳር ዝርያ፣ የፓፓያና 4 መቶ ሺ የስኳር ድንች ቁርጥራጮች እንደሚከፋፈል የተናገሩት ዶ/ር መብራቱ ተጨማሪ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችም የሚሰጡ ይሆናል ብለዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ሥራ ውስጥ እንደ ሀገር የሚስተዋለው የዘር ዕጥረት ትልቅ ማነቆ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው ችግሩን በመገንዘብ በምዕራብ ዓባያ ወረዳ ዛላ ኩትሻ ቀበሌ የድንች ምርጥ ዘር አምራች የአርሶ አደር ማኅበር በማደራጀት ዕውቅና እንዲያገኝ በማድረግ የዘር ማከማቻ መጋዘን ለማኅበሩ እየገነባን ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማኅብረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንትና የአማካሪ ም/ቤቱ አባል ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እንዳሉት ከፕሮጀክቱ ዓላማና ግብ አንፃር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመው በወረዳና በቀበሌ አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች ዘንድ የባለቤትነት ስሜት የመፈጠሩ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ወራት እንደ ቀሩት የተናገሩት ዶ/ር ስምዖን በተገልጋዩ አርሶ አዳርና ዳጋፊ አካላት ዘንድ የባለቤትነት ስሜት ተፈጥሮ ሥራዎቹ ቀጣይነት ሊኖራቸው እንደሚገባና ፕሮጀክቱም የራሱን የመውጫ ስትራቴጂ ሊያዘጋጅ ይገባል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንትና የአማካሪ ም/ቤቱ ሰብሳቢ ዶ/ር አያኖ ባሪሶ በበኩላቸው እንደገለፁት በዋናነት የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ከድኅነትና ተረጂነት መላቀቅ እንችላለን የሚል አመለካከት እንዲኖራቸው ለማድረግ በትኩረት መሠራት እንዳለበት በማሳሳብ ፕሮጀክቱ በሚያበቃበትም ጊዜ ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ለማስቻል የአቅም ግንባታ ሥራዎች ተጠናክረው ሊሠሩ ይገባል፡፡ ፕሮጀክቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በውይይት ወቅት ሐሳባቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች በፕሮጀክቱ እየተሠራ ያለው ሥራ ጠቃሚና የሴፍትኔት ተረጂ አርሶ አደሮችን ከተረጂነት ለማላቀቅ በሚደረገው ጥረት ወስጥ ሚናው ጉልህ ስለሆነ ሥራው የዩኒቨርሲቲዎች ማኅበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራ አካል ሆኖ ጠቃሚነቱ የጎላ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት