ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የሙያ መስኮች በመደበኛ፣ በማታ፣ በክረምት፣ በሣምንቱ መጨረሻ እና በርቀት ያሰለጠናቸውን  3760 በቅድመ ምረቃ እና 88 በድህረ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራሞች በድምሩ 3848 ተማሪዎች ሰኔ 18/2008 ዓ.ም በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል በቅድመ ምረቃ 1044 እና በድህረ ምረቃ 10  ቱ ሴቶች ሲሆኑ ዩኒቨርሲቲው በዓመቱ በአጠቃላይ በቅድመ ምረቃ 5398 እና በድህረ ምረቃ 328 በድምሩ 5726 ተማሪዎችን ለምረቃ አብቅቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዴኤታ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ካባ ኡርጌሳ ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት የሥራ መመሪያ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ በሚከናወነው ህዝብን ተጠቃሚ ያደረገ የልማት እንቅስቃሴ ተመራቂዎች ንቁ ተሳታፊ በመሆን እና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዋነኛ ማነቆ የሆነውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን በፅኑ በመታገል የበኩላቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ አደራ ብለዋል፡፡

ሀገራችን አትዮጵያ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ካስመዘገበቻቸው ድሎች አንዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተደራሽነትና ፍትሃዊ ስርጭት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የከፍተኛ ትምህርት ስርጭትን በማስፋፋት ረገድ በቀደሙት ሥርዓቶች የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በጣት የሚቆጠሩ ከነበሩበት ወደ 35 ያደጉ ሲሆን 11 አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች ደግሞ ግንባታቸው መጀመሩን ገልፀዋል፡፡ ከተደራሽነቱ ጎን ለጎን የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን መንግሥት ከነደፋቸው ስልቶች በተጨማሪ የተማሪው፣ የመምህሩ፣ የወላጆችና የማህበረሰቡ ሚና በእጅጉ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው ያላቸውን ቆይታ በስኬት አጠናቀው ለዚህ ልዩ ቀን በመድረሳቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው በተማሩበት የሙያ መስክ ውጤታማ በመሆን ያካበቱትን እውቀትና ክህሎት ለሀገር ግንባታ እንዲያውሉ አሳስበዋል፡፡

ከዓመቱ አጠቃላይ ተመራቂዎች 2273ቱ የቴክኖሎጂ ኢንስትዩት፣ 48 የህግ ት/ቤት ተመራቂዎችን ጨምሮ 1036 የማህበረሰብና ስነ ሰብ ኮሌጅ፣ 731 የተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ፣ 716 የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ፣ 350 የግብርና ሣይንስ ኮሌጅ  292 የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ እንዲሁም 328ቱ የድህረ ምረቃ ተመራቂዎች ናቸው፡፡

ከየትምህርት ክፍሉ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተመራቂዎች ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ከየኮሌጆቹ የላቀ ውጤት ያላቸው 7 ተመራቂዎች የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ምሩቅ ራሄል ጂማ ከህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ሚድዋይፍሪ ት/ት ክፍል 3.92 በማምጣት ከአጠቃላይ ሴቶች በ1ኛነት ልዩ ተሸላሚ ስትሆን ምሩቅ በለጠ ጴጥሮስ ከግብርና ሣይንስ ኮሌጅ የገጠር ልማትና ግብርና ኤክስቴንሽን ት/ት ክፍል 3.98 በማምጣት የዓመቱ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

ከሀገራችን ቀደምት ዘጠኝ ነባር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት 30 ዓመታት ጥራት ያለው ትምህርትና ሥልጠና በመስጠት በውኃው መስክ በሀገሪቱ ግንባር ቀደም ምሁራንን ያፈራ ሲሆን የዘንድሮ ተመራቂዎችን ጨምሮ ከ35,000 በላይ ምሩቃንን ለሀገር አበርክቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማካሄድ እና ለህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ክህሎቶችና ቴክኖሎጂዎችን በማሸጋገር ወደ ማኅበረሰቡ ዘልቆ ማገልገል የጀመረ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡

በ1979 ዓ.ም በውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ደረጃ ተቋቁሞ 290 ተማሪዎች ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው ዩኒቨርሲቲው በ1996 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ በማደግ አሁን ላይ 6 ልዩ ልዩ ካምፓሶችን በመመስረት በስድስት ኮሌጆች፣ አንድ ኢንስቲትዩት፣ አራት ትምህርት ቤቶችና አንድ የስፖርት አካዳሚ ተዋቅሯል፡፡ በዚህም በ56 የቅድመ ምረቃ እና በ45 የድህረ ምረቃ የሥልጠና መስኮች በአጠቃላይ ከ27 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛው፣ በተከታታይና በርቀት መርሃ ግብር በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡