የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በስሩ ካሉ የማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች ጋር በመቀናጀት “በተፈጠረው እድል ማህበረሰቡን እናገልግል” በሚል ርዕስ በዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የማህበረሰብ ሣምንትን ሐምሌ 2/2008 ዓ/ም በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

በዩኒቨርሲቲውና በባለድርሻ አካላት ቅንጅት የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር መለየትና መፍታት እንዲቻል የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ታዬ ገልፀዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት እንቅስቃሴ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያከናወናቸውን ዝርዝር ተግባራት ያካተተ ጽሑፍ በዳይሬክቶሬቱ የልማት ሥራዎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ኤልያስ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡ በጽሑፉ እንደተመለከተው የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ሥራዎች፣ የችግኝ ሥርጭት፣ የማህበረሰብ ልማት ፕሮጀክት ቀረፃና ትግበራ፣ ዘርፈ ብዙ የማማከርና አጫጭር ስልጠናዎች፣ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት፣ የአርብቶ አደር አካባቢዎች የመስኖ ልማት ስልጠናዎች፣ ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት፣ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን የማስተማር ስነ-ዘዴ የአቅም ግንባታ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የክረምት ማጠናከሪያ ሥልጠናዎች በዳይሬክቶሬቱ ማስተባበሪያዎች አማካኝነት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ብቁ ምሩቃንን በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሀገር ልማት ከማበርከት ባሻገር ህብረተሰቡን ተደራሽ ያደረጉ ችግር ፈቺ ምርምሮችና የማህበረሰብ ግልጋሎቶች በስፋት በማከናወን ላይ ነው፡፡ ለማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በተሰጠው ልዩ ትኩረት በመዋቅሩ ላይ ማሻሻያ በማድረግና የማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች በማደራጀት የልማት ሥራዎች፣ የማማከርና አጫጭር ስልጠናዎች እንዲሁም ነፃ-የህግ ድጋፍ አገልግሎት መስጠት በመቻሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካተኔ ካውሌ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በምርምር የተደገፉ ሥራዎችን ከዞኑ አስተዳደር ጋር በቅርበት በመሥራት የመጀመሪያውን ምዕራፍ በዚህ መልኩ ማስቃኘቱ የሚያስመሰግን ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ ከጋሞ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ እና ሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን አስተዳደር ጽ/ቤቶች እንዲሁም በሦስቱ ዞኖች ከሚገኙ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው አመራር አካላትና መምህራንን ጨምሮ ከ150 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በዳይሬክቶሬቱ የተከናወኑ ተግባራት በባነር ታትመው በአውደ-ርዕይ መልክ ለእይታ የቀረቡ ሲሆን በልማት ሥራዎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አማካኝነት በአካባቢ መልሶ ማገገምና አካባቢ ጥበቃ በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ በሚገኘው ተራራማ ሥፍራ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የመስክ ላይ ጉብኝትም ተደርጓል፡፡

ተሳታፊዎቹ በማህበረሰብ አገልግሎት ዙሪያ ሃሳቦችን የተለዋወጡ ሲሆን በቀጣይ ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር በጋራ የመለየትና የመፍታት ሥራዎችና የጋራ ግንዛቤ መድረኮችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡