በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት 16ኛው ዘላቂ የውሃ ሀብት ልማት ዓውደ ጥናት ከሰኔ 24-25/2008 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል ለመሆን ከሚተጋባቸው መስኮች አንዱ የውሃ ሀብት ልማትና አስተዳደር በመሆኑ ተመራማሪዎችን፣ ውሳኔ ሰጪ አካላትንና ባለሙያዎችን በማቀራረብ ለዘላቂ የውሃ ሀብት ዕድገት አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም የአስተዳደራዊ መዋቅሩን በማደስ የታለመውን ግብ መምታት በሚያስችለው መንገድ በመስራት ላይ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል፡፡
የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ጀምስ ደንግሆል ቶት እንደገለፁት ውሃ ለሰው ልጅ ህልውና፣ ለጤናማ አካባቢና ለተስተካከለ ብዝሃ ህይወት ወሳኝ ቢሆንም በአግባቡ ካልተገለገልንበት የጥቅሙን ያህል ጉዳት ያለው በመሆኑ የውሃ ሀብታችንን በጥንቃቄና በተገቢው መንገድ መያዝ ይኖርብናል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በማደግ ላለው ምጣኔ ሃብትና የህዝብ ቁጥር ተደራሽ የሚሆን ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሟላት እየሠራች ቢሆንም የባለሙያዎች፣ የቴክኖሎጂና የውሃ ሃብት አጠቃቀምን የሚቆጣጠሩ ተቋማት ውስንነት፣ የገንዘብ እጥረት እንዲሁም የፍሳሽ ማስወገጃና የአካባቢ ጥበቃ ችግሮች የዘርፉ ተጠቃሽ ተግዳሮቶች መሆናቸውን የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ገልፀዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ በታዳሽ ኃይል፣ በመስኖ ውሃ አጠቃቀም፣ በከተሞችና በገጠር አካባቢ የመጠጥ ውሃና የፍሳሽ ማስወገድ ስርዓት፣ በተፋሰስ ልማት እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረት ያደረጉ 20 የተለያዩ የምርምር ስራዎች ቀርበዋል፡፡
የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ባለሥልጣን ዳይሬክተር ዶ/ር ከበደ ካንቹላ ባቀረቡት ፅሑፍ እንደጠቆሙት ውሀ ከህዝቦች ህልውና፣ ዕድገት፣ ልማት፣ ጤንነትና ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ይሁንና ይህ ውስን የውሀ ሀብት በብክለት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በደኖችና በእፅዋቶች መመናመን እንዲሁም በመሰል ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች መጠኑና ጥራቱ እየቀነሰ ይገኛል፡፡
በዓለማችን የተለያዩ የውሀ አካላት መጠናቸው እየቀነሰና እየደረቁ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በመሆኑም በሀገራችን ተመሳሳይ ተግዳሮቶችን ከጅምሩ ለመቀነስና ለማጥፋት፣ የውሀ ሀብቱን በዘላቂነት ለማልማትና የግብርና ኢኮኖሚው ለኢንዱስትሪው ሽግግር የሚያደርገውን አስተዋፅኦ በአግባቡ ለመጠቀም የተቀናጀ የውሀ ሀብት አስተዳደር ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ በተፋሰስ ደረጃ የውሀ ሀብቱን የማልማት ስራ እየተከናወነ ነው፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም በሀገራችን የሚገኙ የውሃ ሀብቶች መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን ተከትለው የሚፈሱ በመሆናቸው ለቁጥጥር አመቺ እንዲሆን በተፋሰስ መከፋፈል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልፀዋል፡፡ በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ 12 ተፋሰሶች ያሏት ሲሆን ከተፋሰሶቹም በዓመት 123 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የገጸ ምድር እና ከ30-40 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የከርሰ ምድር ውሀ እንደሚፈስ መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል፡፡
የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ምሁራንን ማሳተፉ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ ተማሪዎችን ማካተት ቢቻል መልካም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በጥናታዊ ጽሑፎቹ ላይ ጥያቄዎችን አንስተውም ከአቅራቢዎቹ ምላሽ አግኝተዋል፡፡