በፌዴራል መንግስት ሠራተኞች አዋጅ  ቁጥር 515/ 1999 አንቀፅ 72 መሠረት ቋሚ የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ ማቋቋም ተገቢ በመሆኑ ከዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሠራተኞች የተወጣጡ 7 አባላትን የያዘ ኮሚቴ ሚያዝያ 26/2008 ዓ/ም ተቋቁሟል፡፡

 

ኮሚቴው ከህጎችና መመሪያዎች አተረጓጎም ወይም አፈፃፀም፣ ከመብቶችና ጥቅሞች አጠባበቅ፣ ከሥራ አካባቢ ጤንነትና ደህንነት፣ ከሥራ ምደባና ደረጃ እድገት አሰጣጥ፣ ከሥራ አፈፃጸም ምዘናና በሥራ ኃላፊ ከሚፈፀሙ ተገቢ ያልሆኑ ተፅዕኖዎች እንዲሁም የስራ ሁኔታዎችን ከሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሠራተኞች የሚያቀርቡትን የቅሬታ አቤቱታ ተቀብሎ በማጣራት የውሳኔ አስተያየት ለመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ የሚያቀርብ መሆኑን የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ተ/ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ ገልፀዋል፡፡

የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት አቶ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ መቋቋም በአንድ መስሪያ ቤት ዴሞክራሲያዊ አካሄዶችንና ግልፀኝነትን ከማስፈን አኳያ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል፡፡ በሠራተኛው ቅጥር፣ ዝውውር፣ የውስጥ እድገትና ሌሎች መሰል የሠራተኛውን ጥቅም የሚያስከብሩና ለውጥ የሚያመጡ ጉዳዮች አፈፃፀም እንዲሁም በአንድ ሠራተኛ ላይ በሚወሰዱ ህጋዊ እርምጃዎች ኮሚቴው ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ የሠራተኛው መብት የሚከበርበት፣ አድሏዊ አሠራር የሚወገድበት፣ ሰዎች በነፃነት ቅሬታቸውንና ሃሳባቸውን ገልፀው የመንግስት ደንብና መመሪያ በሚፈቅደው መሰረት ምላሽ የሚያገኙበት በመሆኑ በሠራተኛው ላይ ሊደርስ የሚችለውን አላስፈላጊ ድካምና ክርክርን የሚቀንስ ሲሆን ይህም በዩኒቨርሲቲው እንደ አንድ የለውጥ መሳሪያ የሚያገለግል ይሆናል፡፡ በቀጣይ ቅሬታን በፍጥነት በማስተናገድና ምላሽ በመስጠት ግልፀኝነት ያለው የአሰራር ሂደት ለማስፈን መመሪያና ደንብን ተከትሎ የተዛቡ አሰራሮችን የማስተካከል ሥራ የሚከናወንና የኮሚቴው አደረጃጀት በሁሉም ኮሌጆች በሂደት የሚስፋፋ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የተመረጡት ኮሚቴዎች መመሪያና አዋጁን በሚገባ መረዳትና በትክክል ማወቅ ይኖርባቸዋል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ በተጨማሪም በቋሚነት እየተሰበሰቡ ህግና ደንቡን በተግባር በመተርጎም የቅሬታ አቤቱታን በአግባቡ እንዲያስተናግዱና ያልተፈቱ ቅሬታዎችን ወደሚመለከተው አካል በማድረስ መፍትሄ እንዲያስገኙ አሳስበዋል፡፡