አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2017 ዓ/ም 1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን ኅዳር 11/2017 ዓ/ም የካውንስል አባላት በተገኙበት ገምግሟል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲውን መሠረታዊ መረጃዎች፣ በሩብ ዓመቱ የታቀዱ ዋና ዋና ስትራቴጂክ ጉዳዮችና አፈጻጸማቸውን እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮች፣ የመፍትሔ እርምጃዎችና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን የዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰሎሞን ይፍሩ ለካውንስሉ አባላት አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት ዩኒቨርሲቲው በዝግጅት ምዕራፍ ትምህርት ከመጀመሩ ቀደም ብሎ የኮርስ ድልድል ሥራ በመሥራትና የonline ምዝገባ ሂደት ለማቀላጠፍ ተማሪዎች በክረምት የወሰዷቸውን ኮርሶችን ለመምህራን በማድረስ የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ትምህርት በወጣው የትምህርት ጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲከናወን መደረጉ ተገልጿል፡፡

የትምህርት ጥራት፣ አግባብነት፣ ተደራሽነትና ፍትሐዊነትን ከማረጋገጥ አንጻር የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ፣ የተማሪዎችና መምህራን የትምህርት ደረጃ ስብጥር፣ የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ እና የድኅረ ምረቃ ትምህርትን ማሳደግ ላይ ዕቅዱን መሠረት አድርጎ መከናወኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

የምርምር እና ፈጠራ ሥራዎች ተደራሽነትና ፍትሐዊነት እንዲሁም የሀገር በቀል ዕውቀትን ማጣጣምና ማሳደግን በተመለከተ በሩብ ዓመቱ 22 ነባር ምርምሮች የተጠናቀቁ ሲሆን ጭብጥ ተኮር ምርምርን በሥራ ላይ ለማዋል ዘጠኝ የምርምር ጭብጦች /Research Thematic Areas/ ተለይተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር የምርምር ሲምፖዚዬምና የትብብር ምርምር ግራንት ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሮችን ማካሄዱ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ 

በሌላ በኩል ለተቋራጮች እና ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የማማከር አገልግሎቶችን መስጠት፣ ነፃ የሕግ ጥብቅና ፣ የምክር አገልግሎትና የሰነድ ዝግጅት ድጋፍ፣ በ‹‹STEM›› ማዕከል የክረምት መርሃ ግብር ተማሪዎችን ማሠልጠን፣ እንዲሁም በተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትና ሥልጠና በደረጃ አንድና ሁለት ጎልማሶችን ማሠልጠን ከማኅበረሰብ ጉድኝትና የሳይንስ ባህል ግንባታ ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን ማሳደግ ጋር ተያይዞ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በዚሁ ዘርፍ በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት በጀመረው የዩኒቨርሲቲው የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሺያላይዝድ ሆስፒታል 1240 ተጠቃሚዎችን የሕክምና አገልግሎት መሰጠቱ  በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

የተቋማት ትስስርና ተሳትፎ፣ ሥራ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ዓለም አቀፍ አጋርነትን ማሳደግን አስመልክቶ በሩብ ዓመቱ አንድ ቴክኖሎጂ ለማኅበረሰቡ የተሸጋገረ ሲሆን አጫጭርና ረዣዥም ሥልጠናዎች፣ የወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ውድድርና ሽልማት እንዲሁም ከሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ኢንደስትሪዎች ጋር የመግባቢያ ሰነዶች ፊርማ ተከናውኗል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዕውቀትና ቴክኖሎጂ የተደገፈ የፍትሕ ሥርዓት ለማስፈን የሚረዳ የፎረንሲክ ምርመራ ማዕከል ሥራ ማስጀመሩም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ የትምህርት አመራርና አስተዳደርን ከማጠናከር አኳያ ዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝ አስተዳደር ትግበራን ለማከናወን ተቋማዊ ራስ ገዝ ፕሮጀክት ጽ/ቤት በማቋቋም ወደ ሥራ የገባ ሲሆን ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ጋር በመሆን የዩኒቨርሲቲውን ሴኔት መተዳደሪያ ደንብና ስትራቴጂክ ዕቅድ የመከለስ ሥራ መጀመሩ ተጠቅሷል፡፡ 

በተጨማሪም የትምህርት ተቋማዊ አቅምና ብቃት ለማጎልበት እንዲሁም የትምህርት መሠረተ ልማትና ፋሲሊቲ እና የሀብት ምንጭና አጠቃቀም ውጤታማነትን ለማሳደግ በሩብ ዓመቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የመምህራን የትምህርት ዕድል፣ የመምህራን አካዳሚክ ማዕረግ እድገት፣ ከሳይት ርክክብ ጀምሮ በተለያዩ ሂደቶች ላይ ያሉ ግንባታዎች ክንውን በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዳምጠው ዳርዛ (ዶ/ር)የአንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸሞች በአብዛኛው የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎች መሆናቸውን ጠቁመው በሪፖርቱ ከዕቅድ በታች የተከናወኑ እና ከመድረኩ እንደ ክፍተት የተነሱ ጉዳዮች በቀጣይ የአፈጻጸም ወቅት በሚገባ አካትቶ መሥራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

የአፈጻጸም ሪፖርቱን የተመለከቱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች አንዲሁም ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ጥቆማ ከተሳታፊዎች የቀረበ ሲሆን በሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የሥራ ክፍል ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ አስቸኳይ የማሻሻያ እርምጃ  የሚሹ ጉዳዮችን አሰመልክቶ ቀጣይ የጋራ ውይይትና ትግበራ ለማድረግም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት