የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል የዩኒቨርሲቲውን የ2017 ዓ/ም ዓመታዊ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ሐምሌ 23/2017 ዓ/ም ገምግሟል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰሎሞን ይፍሩ በስምንት ግቦች የተከፋፈለውን የዩኒቨርሲቲውን የ2017 ዕድቅና የአፈጻጸም ደረጃ ለካውንስሉ አባላት ያቀረቡ ሲሆን የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ፣ የDigital Literacy እና የLMS (Learning Management Systems) አጠቃቀም ሥልጠና፣ የመውጫ ፈተና፣ አዳዲስ የምርምርና ግራንድ ፕሮጀክቶችን መቀበል፣ ዕውቅና ባላቸው ጆርናሎች የምርምር ውጤቶችን ማሳተም፣ ዓመታዊ የምርምር ዐውደ ጥናቶችን ማካሄድ፣ ነጻ የሕግ ድጋፍ እና ሌሎች የማማከር አገልግሎቶች፣ የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት፣ ችግር ፈቺ የማኅበረሰብ ፕሮጀክቶች ትግበራ፣ STEM ማእከል የክረምት ሥልጠና፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የፈጠራ ሃሳቦች፣ የቴክኖሎጂዎች የአእምሯዊ ሀብት ምዝገባ፣ ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር ከሚደረገው ሽግግር ጋር በተያያዘ የሴኔት መተዳደሪያ ደንብና የስትራቴጂክ እቅድ ክለሳ እና ልዩ ልዩ ሰነዶች ልየታ፣ የፕሮግራም አክሬዲቴሽን፣ ግንባታዎችን ማጠናቀቅና እድሳት መልካም አፈጻጸም የተመዘገበባቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የግብዓት ዋጋ መናር፣ የበጀት አለመጣጣም፣ ከሀገር አቀፍ የመግቢያ ፈተና ጋር ተያይዞ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን በበጀት ዓመቱ ከገጠሙ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ዩኒቨርሲቲው በበጀት ዓመቱ እንዲተገብር ከትምህርት ሚኒስቴር የተቀበላቸውን ቁልፍ ተግባራት እና ሌሎች የተጀመሩ ሥራዎችን በስኬት ለመፈጸም በትኩረት ሲሠራ መቆየቱን እና በዚህም በተለያዩ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡ በአንጻሩ ዝቅተኛ አፈጻጸም የተመዘገበባቸውን ዘርፎች በአግባቡ በማጤን የእርምት እርምጃ መውሰድና በቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድ አካቶ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ሪፖርቱን የተመረኮዙ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነሥተው ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በኢትዮጵያ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆነው የተለዩ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ተገኝተው የቀሰሙትን ልምድና ጥቆማዎች የዩኒቨርቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ለመድረኩ አቅርበዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት