የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2018 ዓ/ም የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ጥር 14/2018 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው የስትራቴጂክ ዕቅድ ክትትልና ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ቀርቦ በዩኒቨርሲቲው ካውንስል ተገምግሟል፡፡ ከስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱ ባሻገር ወደ ራስ ገዝነት የሚደረገው ጉዞ ቅድመ ዝግጅትን እንዲሁም የዲጂታል ሊተረሲ አንጻር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ሪፖርትም ቀርቦ ውይይትም ተካሂዷል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ ወደ ራስ ገዝነት ሽግግር የሚያደርግ እንደመሆኑ በርካታ የለውጥ ሥራዎች የሚጠበቁ መሆኑን ተናግረው ይህንን ለማሳካት የሁሉንም የጋራ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት በሁሉም መስክ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ያሉት ፕሬዝደንቱ በበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜያት በተለይ  ቁልፍ ተግባራት ተብለው የተለዩ ዕቅዶችን ለመፈጸም በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል። 

የስትራቴጂክ ዕቅድ ክትትልና ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰሎሞን ይፍሩ ባቀረቡት ሪፖርት የትምህርት ፕሮግራሞችን በበይነ መረብ (Full online modality) መርሐ ግብር ለመክፈት ሁለት የትምህርት ፕሮግራሞች ተመርጠው ቀሪ ሥራዎች እየተከሆኑ መሆኑ፣ የምርምር ማኔጅመንት ኢነፎርሜሽን ሲስተም(ROMIS) እንዲጀምር ተደርጎ የምርምር ስራን በዚሁ መተግበርያ ማከናወን መጀመሩ፣ 473 የምርምር ውጤቶች ዕውቅና ባላቸው ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ መታተማቸው፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅና እንዲያገኙ ሦስት የምርምር ላቦራቶሪዎች ተለይተው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ፣ በነጻ የሕግ አገልግሎት ለ3,582 የማኅበረሰብ ክፍሎች የምክር አገልግሎትና የሰነድ ዝግጅት ድጋፍ መሰጠቱ፣ የተቋማት ትስስርና ተሳትፎ እና ዓለም አቀፋዊነትን በማሳደግ ረገድ 910 ተማሪዎች ለተግባር ትምህርት ሥልጠና (Internship) መውጣታቸው፣ 25 መምህራን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ተቋማት በመምጣት ዕውቀታቸውን እና ልምዳቸውን ማካፈላቸው ተመልክቷል፡፡


የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሮኒክስ ትምህርት ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ አበበ ማዕከሉ በዋናነት 2 ተግባራትን እንደሚያከናውን ገልጸው በመጀመሪያውና ለመምህራን በሚሰጠው ‹‹Master Class Terning (MCT)›› በዩኒቨርሲቲው ካሉት መምህራን 1,370ቱ (ከ91 ከመቶ በላይ) ሥልጠናውን መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡ 2ኛውና ለተማሪዎች የሚሰጠውን ሥልጠና ‹‹Student Success Suite (SSS)›› በተመለከተ ባለፉት ስድስት ወራት 9,277 ተማሪዎች ሥልጠናውን መውሰዳቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ 5 ሚሊየን ኮደርስ ሥልጠናን በተመለከተ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና ተማሪዎችን ጨምሮ 5,700 የሚደርሱ ሥልጠናውን ለመውሰድ መመዝገባቸውንም ጠቁመዋል፡፡  

በዕለቱ የቀረቡ የአፈጻጸም ሪፖርቶችን ተከትሎ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና በሌሎች የዘርፍ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት