የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ሐምሌ 23/2017 ዓ/ም ለካውንስል አባላት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በዕለቱ በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በኢንደስትሪ ትስስርና ማኅበረሰብ ጉድኝት እንዲሁም በአስተዳደር ዘርፎች እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ እና በራስ ገዝነት ለመተዳደር በሂደት ላይ እንዳለ ተቋም መከወን የሚገባቸው ዝርዝር ጉዳዮችን አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲውን ዕቅድ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰሎሞን ይፍሩ አቅርበዋል፡፡

ማሪታይም አካዳሚን በጋራ ማቋቋም፣ ከነባራዊው ሁኔታ በመነሳት በተለይ በበይነ መረብ የማስተማርያ ሞዳሊቲ 2 እና በአካል የሚሰጡትን ጨምሮ በሁለቱም  የትምህርት ፕሮግራሞችን ወደ 22 ማድረስ፣ በ2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጣቸው ፕሮግራሞችን 7 ማድረስ፣ የክረምት ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች በኢመደበኛው መርሐ ግብር የሚማሩ ተማሪዎችን የመውጫ ፈተና የማለፍ ምጣኔ ከመደበኛ ተማሪዎች እኩል በአማካይ ወደ 85 % ማድረስ በዕቅዱ ከተያዙ የመማር ማስተማር ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በሌላ በኩል በምርምና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፎች የምርምር ላቦራቶሪዎችንና የምርምር ማዕከላትን ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ እና አክሬዲቴሽን ማሳደግ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያላቸው ጆርናሎች እንዲኖሩ መሥራት፣ ለዩኒቨርሲቲው ቅርበት ባላቸው ጋሞና ጎፋ ዞንን ጨምሮ ኮንሶ፣ አሌና ቡርጂ በመሳሰሉ አካባቢዎች በማኅበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶች 180 ሺህ የሚሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ፣ በተቋማት ትስስርና ተሳትፎ የቢዝነስ ስታርትአፖችን የአእምሯዊ ንብረት መብት ፈቃድ ማሰጠት፣ እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና ኢንኩቤሽን ማእከል ማጠናከር በዕቅድ ተይዘዋል፡፡

መሠረተ ልማቶችን አስመልክቶ ነባር ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እና የውኃ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ ፓምፕ ተከላና ሌሎችም በትኩረት እንደሚከናወኑ የተመለከተ ሲሆን በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ መደበኛና ካፒታል በጀትን ጨምሮ 3,023,891,530.00 ብር መመደቡ ተገልጿል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት