አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና ሰላም ሚኒስቴር በጋራ በመተባበር ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ሰላምና ጸጥታ ቢሮ እና ከዞኖች ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ለተወጣጡ እንዲሁም ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ጥር 27/2017 ዓ/ም በበጎ ፈቃድ ማኅበረሰባዊ አገልግሎት ጽንሰ ሃሳብ ትግበራና በሀገር ግንባታ መሠረታውያን ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም እንደገለጹት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያለማንም ቀስቃሽ የሚሠራና ለተሰጠው አገልግሎት በምትኩ ምላሽ የማይጠበቅበት የኅሊና እርካታ ሥራ ሲሆን በጎነትን ለማስረጽ፣ የጋራ እሴቶችን ለማጎልበት እና ዘላቂ ሰላምና እድገትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ እንደ ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ሰላም ሚኒስቴር እንደ ሀገር የሰላም እሳቤ በትውልድ አእምሮ ውስጥ እንዲሰርጽ እና ብሔራዊ መግባባት እንዲዳብር ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር በትብብር የሚሠራ ሲሆን ይህን በጎ ዓላማ በመደገፍ በትኩረት ከሚሠሩ ተቋማት አንዱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው የሰላም ሚኒስቴርን የሰላም እሴት ግንባታ ተልእኮ ለማሳካት ተሳታፊ ሠልጣኞችን ተቀብሎ በማስተባበር፣ የመኝታና የምግብ አገልግሎት በመስጠት፣ መምህራንን በማሠልጠንና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ምንነትና ዓላማን በመረዳት ለሀገር ግንባታ፣ ለብሔራዊ መግባባት፣ ለሁለንተናዊ ሰላምና ዘላቂ ልማት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ዜጎችን ለማፍራት ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊና የሰላም ግንባታ የብዝኃነት አያያዥ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በቀለ ሎኮርማ ከዚህ ቀደም መሰል ሥልጠናዎች ለተከታታይ 10 ዙሮች በክልሉ ለሚገኙ ወጣቶች መሰጠታቸውን ገልጸዋል።
ከሰላም ሚኒስቴር የመጡት አሠልጣኞች አቶ ገዛኸኝ ጥላሁን እና አቶ ገመቺሳ ኢቲቻ እንደገለጹት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል አንዱ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር መሥራት ሲሆን በዚህም መሠረት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አግባብነት ያላቸውን አካላት የማስተባበር፣ የመፍትሔ ሃሳቦችን ለመንግሥት የማቅረብና የውሳኔዎችን አፈጻጸም የመከታተል ሥራዎችን እንዲሠራ ይጠበቃል፡፡ በዚህም መነሻ የሀገረ መንግስት ግንባታ(State Building) እና የብሔራዊ መንግሥት ግንባታ(Nation Building) ሥራዎች በተሳካ መንገድ እንዲከናወን ግዙፍ ሀገራዊና ተቋማዊ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሀገራዊ አንድነትና መግባባት የሚያጎለብቱ ስልቶችንና አሠራሮችን ለመተግበር ከሰላም ሚኒስቴርና ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመቀናጀት የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥልጠናው አስተባባሪ መ/ር ተፈራ ቀኝያለው ሥልጠናው በወሰን ተሻጋሪ የተማሪዎች በጎ ፈቃድ አገልግሎት እሳቤ የአፈጻጸም ግምገማና የሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረታውያን ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ተሳታፊን በዕውቀትና በአመለካከት እንዲበቁ በማድረግ ለሀገር ግንባታ፣ ለብሔራዊ መግባባት፣ ለሁለንተናዊ ሰላምና ዘላቂ ልማት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ፣ ሰላምና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ማሳደግ፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎችና በአካባቢው ማኅበረሰብ መካከል አንድነትን ማጎልበት እና የወጣቶችን የምክንያታዊ አስተሳሰብ ክሂሎት መገንባት ከሥልጠናው ዓላማዎች መካል የሚጠቀሱ መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎች የሰላም ባህል ግንባታ፣ የሀገር ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ኢትዮጵያን ከፍ እንደሚያደርግና የሰላም እሴትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በትውልድ አዕምሮ ውስጥ ማስረጽ አስፈላጊ መሆኑን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት