በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ በትምህርት ሚኒስቴር፣ በመቋሚያ የማኅበረሰብ የልማት ድርጅት «MCDO»፣ እና በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ትብብር ሱስና አደንዛዥ ዕፆችን መከላከልና መቆጣጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ አጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት መጋቢት 25/2017 ዓ/ም በጋሞ ባሕል አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የምርምር ጉዳዮች ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል ከሱስና አደንዛዥ ዕፆች ጋር በተያያዘ በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው የትኞቹ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሱስ እንደሚጠቁና ገፊ ምክንያቶችን አስመልክቶ ደቡብ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎችን ያካተት ጥናት ማካሄዱን ገልጸዋል፡፡ የጥናት ውጤቱን ተከትሎ ወጣቶች ከሱስ እንዲወጡ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደ ተቋም እየተሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ተስፋዬ በዘርፉ ከሚሰሩ አጋር ድርጅቶች ጋር ለመስራት ዩኒቨርሲቲው ዝግጁ መሆኑንም አውስተዋል፡፡
የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ውይይቱ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ፣ በትምህርት ቤቶችና በማኅበረሰቡ ዘንድ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና እንደ ሀገር አምራች ዜጎች የሆኑ ወጣቶችን እየጎዳ በመምጣቱ ማኅበረሰባዊ ንቅናቄ በመፍጠር መፍትሔዎችን ማምጣት እንዲቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቶ የጋራ አቅጣጫ ለመያዝ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሪት ብጽዓት ሽመልስ አደገኛ ዕፆችን ማዘዋወርና መጠቀም በአሁን ወቅት በሀገሪቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅሰው ይህንም መቆጣጠርና መከላከል የሚቻለው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ከመሳሰሉ ለሎች አጋር አካላት ጋር በትብብር መሥራት ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዕፅ ዓይነቶች፣ የናርኮቲክስ (Narcotics») ዕፆች፣ የትምባሆ ምንነት፣ ዕፆች በሰዎች ጤና ላይ የሚያስከትሉት ጉዳቶች፣ ወጣቶችና ማኅበረሰቡ በአደንዛዥ ዕፆች ላይ ያላቸው አመለካከትና ግንዛቤ፣ የዕፆች ሥርጭትና ገፊ ምክንያቶች፣ በአደገኛ ዕፆች ተጠቃሚነትና ሱሰኝነት ዙሪያ ቅድም መከላከልና መቆጣጠር እንዲቻል ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ሚና ዙሪያ በዕለቱ ገለጻ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
በውይይቱ ማጠናቀቂያ የውይይቱ ተሳታፊዎች በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ዩኒቨርሲቲው እያስገነባ የሚገኘውን የሱስ ማገገሚያ ማዕከልን የጎበኙ ሲሆን በውይይቱ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከመቋሚያ የልማት ድርጅት፣ ከጋሞ ዞንና ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ አመራሮች፣ መምህራንና የዘርፉ ባለሙያዎች ታድመዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት