በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት ከመጋቢት 27-28/ 2017 / ድረስ ሲካሄድ የቆየው የመንግሥት ዩኒቨሲቲዎች የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎች ፎረም ተጠናቋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በፎረሙ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ እንደ ሀገር ተፈጻሚ እንዲሆኑ ለታቀዱና ተፈጻሚ እየሆኑ ለሚገኙ የሪፎርም አጀንዳዎች ስኬት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽ ሥራ ወሳኝ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም በእንኳን ደኅና መጣችሁ ንግግራቸው እንደገለጹት ያለንበት ጊዜ የመረጃ ፍሰት ፈጣን የሆነበትና ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት በመሆኑ በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የኮሚዩኒኔሽን ሥራ መሪዎች ኃላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም ፎረሙ ዘርፉን አስመልክቶ መረጃዎችን ለመለዋወጥ፣ ግንኙነቶችን ለማጠናከርና ተሞክሮ ለመውሰድ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤቱ በኩል የተለያዩ የውስጥና የውጭ ግንኙነት ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኝ መሆኑን የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ መድረኩ ዩኒቨርሲቲያችን በዘርፉ ያለውን መልካም ተሞክሮ እንዲያጋራ፣ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጠንካራ ሥራዎችን ልምድ እንዲቀስም ብሎም ቀጣይ ዘላቂ ግንኙነቶችን እንዲያጠናክር ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ተፈራ የሀገራችን የትምህርት ዘርፍ ከገጠመው ስብራት እንዲወጣ ለማስቻል በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል በርካታ የሪፎርም አጀንዳዎች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህን ሁሉ አቀፍ የሪፎርም አጀንዳዎች ስኬታማና ውጤታማ ለማድረግ ጠንካራ የሕዝብ ግንኑነትና ኮሚዩኒኬሽን ሥራ ማከናወን ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች እንዚህን የሪፎርም አጀንዳዎች ተክትለው መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የሕዝብና ዓለም አቀፍ  ግንኙነት መሠረታዊ ሃሳቦች በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረበት በትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ቦጋለ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ተቋም  ራዕይውን፣ ዓላማዎቹንና የሚከናውናቸውን ተግባራት ለመሸጥ የሚጠቀምበት በዕቅድ የሚመራ መዋቅር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ለአንድ ተቋም ስኬት ወሳኝ ሚና ያለው ዘርፍ መሆኑን ያስረዱት ሥራ አስፈጻሚው የፈረሙ ተሳታፊ ኃላፊዎች ሙያቸውን በሚገባ አውቀው የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ አበርክቶና ሚና መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣና ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሳምሶን መኮንን ‹‹Contemporary PRs Communication Strategy›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ገለጻ  ዘመኑ የቴክኖሎጂና የኮሚዩኒኬሽን እንደ መሆኑ ሚዲያ ላይ ራሱን ያለሸጠና በሚዲያ የተሸነፈ ሀገርም ሆነ ተቋም የትም መድረስ አይችል ብለዋል፡፡ ከዚህ አንጻር በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ኃላዎች ከሚዲያዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር፣ የገጽታ ግንባታ ስትራቴጂ ማዘጋጀት፣ የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞችን መጠቀምና በየጊዜው ወቅታዊ ማድረግ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞችን ቬሪፋይ ማስደረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን የዘርፉን ልምድ እንዲሁም ተቋሙ በመማር ማስተማር፣ ምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ያከናወናቸውን ተግባራት በዩኒቨርሲቲው ምርምር ጉዳዮች ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም በኩል የቀረበ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ዩኒቨርሲቲውን የሚያስተዋውቁ ሥራዎችን የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሆኖ ከተመሠረተበት 1979 ዓ/ም ጀምሮ ውኃ ምኅንድስናን ጨምሮ በሌሎች በርካታ ዘርፎች ሀገርን፣ ተቋማትን፣ ፕሮጀክቶችን የመሩ ኃላፊዎችን ጨምሮ በርካታ ምሁራንን ለሀገር ያበረከት ተቋም መሆኑን ዶ/ር ተስፋዬ በገለጻቸው ጠቅሰዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ምርምር ተኮር የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥረዎች እየከናወነ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ተስፋዬ የእንሰት ምርት ማቀነባበርና ማብላላት ሂደትን በማዘመን ረገድ የተሰሩና መሬት የወረዱ ሥራዎች፣ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የተከናወኑና ማኅበረሰቡ ጋ የደረሱ ተግባራት፣ በማዕድን፣ በነጻ የሕግ ድጋፍ፣ በተፈጥሮአዊ ማዳበሪያ ዘግጅት ወዘት የተከናወኑ ተግባራትን ለአብነት አንስተዋል፡፡

የፈረሙ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በመድረኩ የሁለት ቀናት ቆይታ በርከት ያሉ አዳዲስ ተሞክሮዎች የቀሰሙበት፣ እርስ በእርስ ልምድ የተለዋወጡበት፣ ከቀረቡ ገለጻዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሕዝብ ግንኙነት ሥራን ለማጠናከርና የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚያስችሉ አዳዲስ ዕውቀቶችን ያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ፎረሙ በተሳካ ሆኔታ እንዲካሄድ ላደረገው የላቀ ሚና ምስጋናቸውን ችረዋል፡፡

በፈረሙ ከላይ ከተጠቀሱ ገለጻዎች ባሻገር ‹‹Leveraging Digital Mass Media for Public Relation››፣ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከKPI ስኬት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ ሚናና ኃላፊነት ፣ የመረጃ ነጻነት ሕግ ትገበራ በሚሉ ርዕሶች ተጨማሪ ገለጻዎች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን በመድረኩ ማጠቃላይ የፎረሙ ተሳታፊዎች የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማርያና ኮምፕርሄንሲቭ ሆስፒታልንና የአርባ ምንጭ አዞ እርባታ ጣቢያን ጎብኝተዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት